የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከ45 በላይ ከሚሆኑ ከተለያዩ የአፋሪካ ሀገራት ከተወጣጡ የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ብሔራዊ ማኅበራት ጋር ምክክር እያካሄደ ይገኛል።
ምክክሩ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የተለያዩ በጎ አድራጎት ማህበራት በተሳተፋበት በዚህ ጉባዔ፤ የሀብት አሰባሰብ ልምድ ልውውጥ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር እና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር እየተካሄደ ነው።
በምክክር መድረኩ የተለያዩ ሀገራት ያላቸውን ተሞክሮ ያጋሩ ሲሆን የኢትዮጵያ የቀይ መስቀል ማኅበር እያከነወናቸው ያሉ ተግባራትን በማስመልከት የማኅበሩ ዋና ፀሐፊ አበራ ሉሌሳ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ማኅበሩ 90 ዓመታትን የተሻገረ መሆኑን አንስተው፤ ማኅበሩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ከማድረስ በተጨማሪ፣ ተቋማትን የማቋቋም ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ማኅበሩ በራስ አቅም ለመተዳደር በተለያዩ ቦታዎች ያሉትን ህንፃዎች በማከራየት እና ገቢ በማመንጨት፣ ባለው የእርሻ መሬቶች ላይ በማምረት እና የአባላትን ቁጥር በማሳደግ ከውጭ የሚገኘውን እርዳታ ለመቀነስ እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በመድረኩ ከተለያዩ አፍሪካ ሀገራት የተገኙ የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማኅበራትም ልምዳቸውን ያጋሩ ሲሆን፣ መድረኩ ያለውን አቅም ለማጠናከር እንደሚረዳም ተመላክቷል፡፡
በሂሩት እምቢአለ