የሰው ልጅ መገኛ፣ የስልጣኔ መናገሻ፣ የተወዳጅ ጣዕም ባለቤት የሆነው ቡና መፍለቂያ የሆነችው ኢትዮጵያ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት መሆኗ እስኪዘነጋ በ1960ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በድህነትና በጦርነት ስሟ ተደጋግሞ በነጮች አፍ ዋለ።
ኢትዮጵያ ሲባል በአፍሪካ በማር ምርት እና በቀንድ ከብት ብዛት አንደኛ መሆኗ ተረስቶ፤ ጣፋጭ ቡና ከጓሮዋ ሸምጥጣ ለዓለም ማጠጣቷ ተዘንግቶ፤ ከሶስት ሺህ ዓመታት በፊት ዓለምን በስልጣኔ ቀድማ እንደነበር ተዳፍኖ ስሟ በክፉ ይጠራ ያዘ።
ታዲያ ይህን ስም በደግ የሚቀለብሱ ልጆቿ በስፖርቱ ዓለም ብቅ አሉ።
በ1960 በሮም ኦሎምፒክ ዓለም አዲስ ጀግናን በሩጫው ሜዳ ተዋወቀች፤ እርሱም ኢትዮጵያዊው ጀግና አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ ነበር።
በባዶ እግሩ በመሮጥ የማራቶን ሻምፒዮን የሆነው አበበ ቢቂላ፤ በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት የመጀመሪያው አፍሪካዊም ነው።
ክፋው በደግ ተሻረ፤ ኢትዮጵያ የጀግናው፣ የአልበገር ባዩ የሻምበል አበበ ቢቂላ ሀገር በመባል መጠራት ጀመረች።
ይህን በደግ መጠራት ቀድማ የሰማች ኢትዮጵያዊ ከተማም፣ ሀገራችን በክፉ ስሟ እንዳይጠራ አበበን የመሰሉ፣ ለባንዲራ ሚዋደቁ ጀግኖችን ታፈራ ያዘች።
ስሟም የኢትዮጵያ ሰንደቅ መስቀያ ማማ ተባለ።
ይህቺ ከተማ እግራቸው ለባንዲራቸው ክብር ሲሆን በእጥፍ የሚዘረጋ፤ ለሰንደቋ ፍቅር ከዓይናቸው እንባ የሚቀድም አትሌቶች መብቀያ በቆጂ ናት።
የአትሌቲክስ ስፖርት ዘርፍ ሲታወስ ሁሌም ስሟ ቀድሞ የሚነሳ እና የወርቃማ ባለድል አትሌቶች መብቀያ የሆነችው በቆጂ ከተማ የተመሰረተችው በ1929 ዓ.ም ነው።
3,409 ሄክታር ስፋት ያላት በቆጂ ከተማ የኢትዮጵያ ሰንደቅ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ እና ኢትዮጵያውያን በአንድነት በአሸናፊነት ክብር ሃሴት እንዲያደርጉ ምክንያት ሆናለች።
ከባርሴሎና እስከ ለንደን እና ኦሪገን ድረስ የኢትዮጵያ ክብር እና ሰንደቅ ከፍ ብሎ የታየበት ገድል ምክንያት የሆኑ አትሌቶች ከዚህች ከተማ የተገኙ ናቸው።
በቆጂ ኗሪዎቿ በአብሮነት እና በፍቅር የሚኖሩባት፣ ሰላማዊት እና ለጤና ተስማሚ ምቹ አየርን የታደለች፤ በዙሪያዋ በሚገኙ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ለስፖርተኞች ጠቃሚ እንደሆነ የሚነገርለት ገብስ በስፋት የሚመረትባት ከተማ ናት።
በፋጡማ ሮባ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና ትኪ ገላና አማካኝነት 10 የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ለአገራቸው ማምጣት የቻሉ አትሌቶችን አፍርታለች።
ላለፉት 20 ዓመታት ከ32 በላይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ላይ ከ10 በላይ የዓለም ክብረወሰኖችን ማሻሻል የቻሉ አትሌቶች መፍለቂያ ነች - በቆጂ።