የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) 'የመደመር ትውልድ' መጽሐፍ በፓኪስታን ብሔራዊ ቋንቋ (ኡርዱ) ተተርጉሞ ለንባብ ቀርቧል፡፡
በኢትዮጵያ እና በፓኪስታን መካከል እየተጠናከረ የመጣውን የባህል ትስስር ተከትሎ፣ መጽሐፉ በፓኪስታን ብሔራዊ ቋንቋ ማስተዋወቂያ መምሪያ አማካኝነት የትርጉም ሥራው ተጠናቅቆ ለንባብ መብቃቱ ተገልጿል፡፡
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) የተተረጎመውን መፅሐፍ ባስመረቁበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የመጽሐፉ መተርጎም በፓኪስታን በሚገኙ የፖለቲካ ሊሂቃን፣ ምሁራንና ወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈውን የመደመር ፍልስፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኡርዱኛ ተናጋሪዎች በቀጥታ ከምንጩ እንዲረዱ ያስችላል፡፡
አክለውም ኢትዮጵያ የምትከተለውን የጋራ ብልጽግና አስተሳሰብ ለማስተዋወቅ መጽሐፉ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት፡፡
መጽሐፉ በፓኪስታን በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ቤተ-መጻሕፍት እና የምርምር ተቋማት እንደሚያሰራጭ የፓኪስታን ብሔራዊ ቋንቋ ማስተዋወቂያ መምሪያ አስታውቋል፡፡
ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የእውቀትና የልምድ ልውውጥ ወደ ላቀ ደረጃ ያደርሰዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የመጽሐፉ መተርጎም የኢትዮጵያና ፓኪስታን ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ፍሬ ማሳያ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ለቀጣይ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር መሰረት የሚጥል ታሪካዊ ክስተት ሆኖ መመዝገቡም ተመላክቷል።