ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቱርክዬው ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን ጋር ባደረጉት ፍሬያማ ውይይት፣ ኢትዮጵያ እና ቱርክዬ በፀረ-ሽብር ትግሉ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከፕሬዚዳንት ኤርዶዋን ጋር በሰጡት መግለጫ፥ ቱርክዬ 31ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ጉባዔ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ 32ኛውን ጉባዔ ለማዘጋጀት ባለባቸው ዕቅድ ዙሪያ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እና ለመደጋገፍ መግባባታቸውን ገልጸዋል።

አፍሪካ በሚቀጥሉት ዐሥርት ዓመታት የሚገባትን ስፍራ እንድትይዝ በሚደረገው ጥረት ውስጥ፣ የእስያ እና አውሮፓ አገናኝ የሆነችው ቱርክዬ ሚና ላቅ ያለ ስለመሆኑም መግባባት ላይ መደረሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ እና ቱርክዬ የረጅም ጊዜ ወዳጅነት በመከባበር እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ተመስርቶ ይበልጥ እንዲጠናከር ስምምነት ላይ መደረሱንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አረጋግጠዋል።
ፕሬዚዳንት ኤርዶዋን የኢትዮጵያን የቀጣናዊ ትስስር ሚና በመገንዘብ፣ ለሁለንተናዊ ድጋፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት መግለጻቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በለሚ ታደሰ
#Ethiopia #Turkiye #CounterTerrorism #SecurityCooperation #RegionalPeace #HornOfAfrica #COP31 #COP32 #EthiopianBroadcastingCorporation #EBC #EBCdotstream