Search

ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ችግር የመፍትሔው አካል የሆነችው ኢትዮጵያ

ሰኞ ኅዳር 08, 2018 177

ኢትዮጵያ ተፈጥሮን በመንከባከብ ዘመናትን ያስቆጠረ ሰፊ ተሞክሮ አላት።

የቅርቡን ብንጠቅስ፥ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያከናወነችው የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ የ2027 የዓለም አየር ንብረት ጉባዔን (cop32) እንድታዘጋጅ አስመርጧታል።

ከቆየው ለአብነት ብናነሳ፥ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጉራጌ ዞን ተፈጥሮን በመንከባከብ ረገድ የቆየ ተሞክሮ ያለው ነው።

በንግዱ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሚታወቀው የጉራጌ ማህበረሰብ፣ ተፈጥሮን መንከባከብም ሌላው መለያው ነው።

የጉራጌ አባቶች ለትውልድ የሚያስተላልፉት ሀብት ንብረትን ብቻ ሳይሆን፣ ጥብቅ ተፈጥሮን ጭምር ነው።

ለዚህ ጥሩ ማሳያ ከ600 ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ የሚነገርለት እና በጉራጌ ዞን፣ እዣ ወረዳ የሚገኘው የቆጠር ገድራ ጥንታዊ ጥብቅ የተፈጥሮ ደን ነው።

ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተውጣጣ የጋዜጠኞች ቡድን፣ 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ፣ በቆጠር ገድራ ጥንታዊ ጥብቅ የተፈጥሮ ደን ጉብኝት አድርጓል።

የቆጠር ገድራ ጥንታዊ ጥብቅ የተፈጥሮ ደን በውስጡ የተለያዩ የዕፅዋት ዓይነቶችን የያዘ ሲሆን፤ ለበርካታ ዘመናት ከሰው ንክኪ ተጠብቆ የቆየም ነው።

ይህ ደን የጉራጌ አባቶች ልክ እንደ ልጃቸው በመንከባከብ ለትውልድ ጠብቀው ያቆዩት ነው።

የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሠረት አመርጋ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት፥ በሥራ ወዳድነቱ የሚታወቀው የጉራጌ ማኅበረሰብ ከተፈጥሮ ጋር ትልቅ ቁርኝት አለው።

ማኅብረሰቡ ለዓለም ስጋት እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ይህን ጥንታዊ ደን በባህሉ መሠረት ጠብቆ ማቆየቱ ለተፈጥሮ የሚሰጠውን ትልቅ ቦታ የሚያሳይ ነው።

በአካባቢው መሠረተ ልማትን በማስፋፋት ደኑ በዘላቂነት ተጠብቆ አማራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን እና ማኅበረቡም በተለያየ መልኩ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን ወ/ሮ መሠረት ተናግረዋል።

እንደዚህ ዓይነት ጥብቅ ደኖች ሥነ ምሕዳርን በመጠበቅ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን ለመከላከል ያላቸው ጥቅም የላቀ ነው ያሉት ኃላፊዋ፤  የቆጠር ገድራ ማኅበረሰብ ተፈጥሮን በመንከባከብ ላሳየው ቁርጠኝነት አድናቆት እና ምስጋና ቸረዋል።

በሃይማኖት ከበደ

#ebcdotstream #climatechange #Ethiopia