Search

እስራኤል በቴክኖሎጂ ፈጠራ እና ግብርናን በማዘመን ያላትን የካበተ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማጋራት ዝግጁ መሆኗን ገለጸች

ማክሰኞ ጥቅምት 11, 2018 60

የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ከዓለም ባንክ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ስብሰባዎች ጎን ለጎን ከእስራኤል የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
አቶ አሕመድ በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር ያላትን በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
የእስራኤል የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች በበኩላቸው ኢትዮጵያ እያደረገችው ያለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ አድንቀው፤ እስራኤል የኢንቨስትመንት ልውውጥን በማበረታታት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማስፋት እንደምትፈልግ ገልጸዋል።
ሀገራቸው በቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ በዲጂታል ፋይናንስ፣ በውሃ ሀብት አስተዳደር፣ በመስኖ እና ግብርናን በማዘመን ያላትን የካበተ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማጋራት ዝግጁ መሆኗንም ተናግረዋል።
በሚኒስትሮቹ መካከል የተደረገው ውይይት የሁለቱን ሀገራት የቆየ ትስስር በጎለበተ ኢኮኖሚያዊ እና የኢንቨስትመንት ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ዕድል የፈጠረ እንደነበር የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስቴር ገልጿል።
በነስሩ ጀማል