Search

IMF የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ለውጥ እና የዕዳ ማስተካከያ ዘላቂ ጥረቶች ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው - ሚስ ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ

ሓሙስ ጥቅምት 13, 2018 97

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ለውጥ እና የዕዳ ማስተካከያ ዘላቂ ጥረቶች ከዋና ዋና የልማት አጋሮች ጋር በቅርበት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ሚስ ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ገለጹ።
እ.አ.አ በኦክቶበር 2025 እየተካሄዱ ካሉት የዓለም ባንክ ቡድን እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) ዓመታዊ ስብሰባዎች ጎን ለጎን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ዋና ዳይሬክተር ሚስ ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ እና ከIMF የአፍሪካ ዲፓርትመንት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አካሂደዋል።
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው የኢኮኖሚ ሪፎርም እና የወደፊት ትብብር ላይ ባተኮረው ውይይት ላይ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ብናልፍ አንዱዓለም እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፍተኛ አማካሪ አቶ ተክለወልድ አጥናፉን ጨምሮ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን አባላት ተሳትፈዋል።
አቶ አሕመድ ሽዴ IMF ለኢትዮጵያ ለሚያደርገው ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸው፣ መንግሥት የፊስካል አስተዳደርን ለማጠናከር፣ የሀገር ውስጥ ሃብት ማሰባሰብን ለማጎልበት እና ቁልፍ መዋቅራዊ የሪፎርም ሥራዎችን ለማፋጠን ያለውን ቁርጠኝነት አፅንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከIMF ጋር ላላት የቆየ አጋርነት ከፍ ያለ ግምት ትሰጣለች ያሉት አቶ አሕመድ፣ በማክሮ ኢኮኖሚ ማረጋጋት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል ላይ ያተኮሩ ደፋር የሪፎርም ሥራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሆነ አስረድተዋል።
የIMF ቴክኒካል እና ፋይናንሺያል ድጋፍ እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት አጋዥ ሆኖ እንደቀጠለም ገልጸዋል።
እየተካሄደ ባለው የሪፎርም ማዕቀፍ ውስጥ ሰፊ የሶሻል ሴኩሪቲ (የማኅበራዊ ጥበቃ) እርምጃዎች አካል በመሆን የኢትዮጵያን አዎንታዊ የኢኮኖሚ ዕይታ እና የመንግሥት የማኅበራዊ ወጪ መጨመርን በተመለከተ ለዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያን የለውጥ ጥረቶች ግስጋሴ እና ስኬት በማጉላት፣ ለስኬቶቹ መነሻ የሚሆኑ በርካታ ቁልፍ ጉዳዮችን አብራርተው፣ ለስኬቶቹ መነሻ የሆኑ ተግባራትን በዝርዝር አስቀምጠዋል። እነዚህም፡-
• በከፍተኛ የመንግሥት እርከኖች ጠንካራ ባለቤትነት እና ቁርጠኝነት፣
• በሁሉም የመንግሥት አካላት ሁሉን አቀፍ ውሳኔ አሰጣጥ እና ትግበራ፣
• በጥንቃቄ የተነደፉ ቅደም ተከተል ያላቸው የሪፎርም እርምጃዎችን በሚገባ ማዘጋጀት፣
• በጣም ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውጤታማ የግንኙነት እና የሶሻል ሴኩሪቲ ዘዴዎች።
• ከልማት አጋሮች በተለይም ከIMF፣ ከዓለም ባንክ እና ከኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ ጠንካራ እና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ዋና ዋናዎቹ ተጠቃሽ እርምጃዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም፥ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳዋን የበለጠ ለማራመድ የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም እና ዘላቂነት ፋሲሊቲ (Resilience and Sustainability Facility /RSF/) ለማግኘት ያላትን ከፍተኛ ፍላጎት አፅንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፥ የሁለትዮሽ እና የንግድ አበዳሪዎች ጋር እየተደረገ ስላለው የዕዳ አያያዝ ውይይቶች ወቅታዊ መረጃዎችን ሰጥተዋል።
በመረጃቸውም እስካሁን የተገኘውን አበረታች ዕድገት በመጥቀስ በዚህ ሂደት ውስጥ የIMF ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አስፈላጊነትን አፅንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
የዓለም ገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሚስ ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ፥ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በIMF ለሚደገፈው የሪፎርም ፕሮግራም ጠንካራ ትግበራ ያላቸውን ቁርጠኝነት በማድነቅ ምስጋና አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ የተሠሩ የሪፎርም ሥራዎች ጉልህ ስኬቶችን ስለማስመዝገባቸው እውቅና ሰጥተዋል።
በዚህም ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገት መመዝገቡን እና የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ መሄዱን ጠቁመው፣ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማጠናከር መንግሥት የጀመራቸውን የሪፎርም ሥራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል እና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲጠናከር ዋና ዳይሬክተሯ እንደሚያበረታቱ ገልጸዋል።
ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ IMF የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ለውጥ እና የዕዳ ማስተካከያ ዘላቂ ጥረቶች ከዋና ዋና የልማት አጋሮች ጋር በቅርበት ለመደገፍ የዓለም ገንዘብ ድርጅት ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
በፈረንጆቹ ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ሊጀመር በታቀደው አራተኛው የፕሮግራም ግምገማ ወቅት ሁለቱም ወገኖች ትብብርን የበለጠ ለማጠናከር እና ዕድገትን እና የማሻሻያ ዕድሎችን በጋራ ለመገምገም ቃል ገብተው ውይይቱ መቋጨቱን በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል።