Search

በሶስት ወራት ብቻ 6.5 ትሪሊዮን ብር የተንቀሳቀሰበት የዲጂታል ፋይናንስ

ሓሙስ ጥቅምት 13, 2018 34

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የመቶ ቀን እቅድ ግምገማ የዓለምን የኢኮኖሚ አዝማሚያ፣ የኢትዮጵያን ማክሮ ኢኮኖሚ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀም እንዲሁም የእድገት አዝማሚያን እና አጠቃላይ ምልከታን ያካተተ አቅርቦትን አካትቷል።
በዓለም የኢኮኖሚ ልማት አውድ ስንመለከት ኢትዮጵያ ልዩ ጥንካሬ እና የእድገት ፍጥነት አሳይታለች ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በ2017 የበጀት አመት የኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ አፈፃፀም በጥንካሬው በመቀጠል 9.2 በመቶ አመታዊ የGDP እድገት ማሳየቱም ተገልጿል።
ይኽም 7.3 በመቶ በሆነ ጠንካራ የግብርና ውጤት መስፋፋት፣ በ13 በመቶ የኢንደስትሪ እድገት ብሎም በ7.5 በመቶ የአገልግሎት ዘርፍ እድገት የተገለፀ ነበር ብሏል ጽህፈት ቤቱ።
የሀገራችን የGDP ተዋፅኦም በብዝኃ መሠረት እየያዘ መሄዱን የሚያሳይ ሲሆን ይኽም በግብርና 31.3 በመቶ፣ በኢንደስትሪ 30.2 በመቶ እና በአገልግሎት 39.6 በመቶ አስተዋፅኦ የታየ መሆኑ ተመላክቷል።
እየተካሄዱ በሚገኙ የለውጥ ሥራዎች፣ በመንግሥት እየተከወኑ ባሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እና አዲስ ኢንቨስትመንቶች በመደገፍ በ2018 ዓመተ ምኅረት ኢኮኖሚያችን በ10.2 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
እንደ የታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ብሎም እንደ የማዳበሪያ ማምረቻ እና የተፈጥሮ ጋዝ ልማት ሥራ ጅማሮዎች የኢኮኖሚ እድገቱን የበለጠ እንደሚያነቃቁ ይጠበቃል። የየዘርፉ የእድገት ትንበያም ጠንካራ ውጤት እንደሚገኝ ያመለክታል።
ግብርና በ7.8 በመቶ፣ በአዳዲስ የማኑፋክቸሪንግ ፕሮጀክቶች እና የተሻሻሉ ግብዓቶች የተጠናከረው ኢንደስትሪ 13.2 በመቶ እንደሚያድጉ የተተነበየ ሲሆን ማዕድን ለ2018 የተቀመጠለትን ግብ እንደሚበልጥ ይጠበቃል ብሏል።
በተጨማሪም የአገልግሎት ዘርፉ እድገት በሚያሳዩት የንግድ እንቅስቃሴ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የቱሪዝም ፍሰት እና የዲጂታል ኢኮኖሚ መስፋፋት በመጠቀም 9.3 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል ሲል ገልጿል።
የውጭ ንግድ 2.5 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን ይኽም እቅዱን እና የባለፈውን አመት ተመሳሳይ ጊዜ አፈፃፀም የበለጠ ሆኖ መታየቱ ተመላክቷል።
የፋይናንስ ዘርፉ የልማት ሥራዎችን እና ኢንቨስትመንትን በመደገፍ እና ቁልፍ ሚናውን እየተወጣ ሲሆን በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 113 በመቶ የሆነ ከቀደመው ተመሳሳይ ጊዜ ብልጫ ያለው የብድር አቅርቦት አቅርቧል ብሏል።
የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትም እየተጠናከረ መሄዱን የቀጠለ ሲሆን በሶስት ወራት ብቻ 6.5 ትሪሊዮን ብር የተንቀሳቀሰበት ደረጃ ደርሷል ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገልጿል።
አጠቃላይ አፈፃፀሙ በሁሉም መስኮች የተሻለ ውጤትን የሚያሳይ ሲሆን ይኽም ኢትዮጵያ ወደ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ብሎም ዘላቂ እና አካታች የኢኮኖሚ እድገት የምታደርገውን ፈጣን ሂደት የሚያረጋግጥ መሆኑ ተመላክቷል።