Search

አየር መንገዱን እንደ ዓይን ብሌን የመጠበቅና የመደገፉ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል- ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

ማክሰኞ ታኅሣሥ 07, 2018 30

የመደመር መንግሥት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ ዓይን ብሌን የሚያደርገውን ጥበቃና አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ።
ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ይህንን ያሉት አየር መንገዱ በ16 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያስገነባውንና የቢዝነስ፣ የፕላቲኒየምና የብር ደረጃ ደንበኞችን የሚያስተናግደውን ባለ ሁለት ፎቅ ዘመናዊ የፕሪሚየም ላውንጅ ዛሬ በመረቁበት ወቅት ነው።
 
ዋና አዛዡ አክለውም፤ አየር መንገዱ በአፍሪካ ያስመዘገበውን ስኬት ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ ራዕይ ሰንቆ እየተጋ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዛሬ የተመረቁት ፋሲሊቲዎችም ለደንበኞች የተሻለ ምቾት እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ እንደሚረዱም አመላክተዋል።
አየር መንገዱ ከአቻ ተቋማት የላቀ አፈጻጸም በማስመዝገብ ሽልማቶችን እያሸነፈ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቱ እንዲጠናከር በሰው ኃይል ልማትና በመሠረተ ልማት ግንባታ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
በቀጣይነት የሚደረጉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችም የአየር መንገዱን የከፍታ ጉዞ በተሻለ አቅም የሚያስቀጥሉ መሆናቸውንም ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ተናግረዋል።
 
በላሉ ኢታላ