Search

የኢትዮጵያና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የአፍሪካ ሕንድ ግንኙነትን ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው

ማክሰኞ ታኅሣሥ 07, 2018 44

 
የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ ከታኅሳስ 7 እስከ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ታሪካዊ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛል፡፡
ይህም የሁለቱን ሀገራት የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው ሲል የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።
ጉብኝቱ ኢትዮጵያ በሕንድ የአፍሪካ ፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ ያላትን እየጨመረ የመጣውን የኢኮኖሚ ትስስር፣ የሁለገብ ልማትና ስትራቴጂካዊ ትብብር፣ እንዲሁም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን የሚያጎላ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር ዋንኛ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከል መሆኗን ያረጋግጣል ብሏል አገልግሎቱ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት ከተለመደው የዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ባለፈ ሕንድ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር እና የዓለም አቀፉን የደቡብ ድምፅ በጋራ ለማጉላት ያላት ፍላጎት መጨመሩንም እንደሚያሳይ ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያና ሕንድ በዘመናዊ ዲፕሎማሲ ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ ግንኙነት የጀመሩ ቢሆንም፣ ሀገራቱ ከ2 ሺህ ዓመት በላይ የዘለቀ ጥልቅ ታሪካዊ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ስለመሆናቸው የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
ሕንድ ኢትዮጵያን በአፍሪካ እና በሰፊው ዓለም መካከል እንደ ድልድይ አድርጋ በማስቀመጥ በአስተዳደር፣ በኢኮኖሚ ልማት፣ በንግድ ዘርፍ፣ በመሠረተ ልማት እና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን በመደገፍ ዘላቂ ወዳጅነቷን አሳድጋለች፡፡
ሕንድ ከአፍሪካ በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰላም ማስከበር እና በዘላቂ ልማት ባሉ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለማጠናከር ፍላጎቷ ከፍተኛ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት የሀገራቸው ቁርጠኝነት ከፍተኛ መሆኑን ያመላክታል ሲል አገልግሎቱ ጠቁሟል።
ሕንድ የኢትዮጵያ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲያድግና የጋራ ተጠቃሚነቷ እንዲረጋገጥ አጋዥ የሆነውን የብሪክስ አባል የመሆን ጥያቄ ከደገፉ አባል ሀገራት አንዷ መሆኗን አገልግሎቱ አስታውሷል። በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት መሻሻል በትብብር እየሠራች መሆኑን አመላክቷል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር በዋና ዋና ዘርፎች በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በታዳሽ ኃይል ትብብር፣ በአቪዬሽን እና በዲጂታል ሽግግሮች ዙሪያ ፍሬያማ ምክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ብሏል፡፡
ጉብኝቱም ከሁለትዮሽ ግንኙነቶች ባለፈ ኢትዮጵያ በበርካታ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እያደገ የመጣውን ተደማጭነቷን የሚያሳይ እና ከዓለማችን 10 ግዙፍ ኢኮኖሚ ከገነቡ ሀገራት አንዷ የሆነችው ሕንድ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ማዕከል አድርጋ መቀበሏን ማሳያ ነው ሲል የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።