በሲዳማ ክልል ተግባራዊ የተደረገው የትምህርት ተሃድሶ ፕሮግራም የመማር ማስተማር ሥራው ላይ ከፍተኛ መነቃቃትን መፍጠሩን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
የሲዳማ ክልል ትምህርት ቢሮ ዓመታዊ የትምህርት ጉባዔ በፈጠራ ሥራዎች ኤግዚቢሽን እና በፓናል ውይይት በሐዋሳ ከተማ ተካሂዷል።

አቶ ደስታ በዚሁ ወቅት፥ በክልሉ ባለፉት 5 ዓመታት በተቀናጀ የህዝብ ተሳትፎ የተተገበረው የትምህርት ተሃድሶ ፕሮግራም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከፍ በማድረግ እና ግብዓት በማሟላት የመማር ማስተማር ሥራው ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲሻሻል ማስቻሉን ገልጸዋል።
በክልሉ ለመማር ማስተማር ሥራው በተሰጠው ትኩረት በ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ሀገር አቀፍ ፈተና አጠቃላይ የማለፍ ምጣኔ በ2014 ዓ.ም ከነበረበት 7 በመቶ አሁን ላይ 15 በመቶ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።

የትምህርት ተሃድሶ ፕሮግራሙ ምቹ የመማሪያ አካባቢን በመፍጠር የትምህርት ጥራትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ መሠረት የተጣለበት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ ናቸው።
በዓመታዊ የትምህርት ጉባዔው በ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች፣ ትምህርት ቤቶች እና መዋቅሮች እውቅና እና ሽልማት ተሰጥቷል።
በአስረሳው ወገሼ
#EBCdotstream #Sidama #education #conference #ትምህርት