የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ማዕከላዊ ባንኩ እያከናወናቸው ያሉ የሪፎርም ስራዎች፣ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያ እና አጠቃላይ የባንኩ ዘርፍ ያለበትን ቁመና በተመለከተ ከኢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ዋጋን ማረጋጋት ከብሔራዊ ባንክ ቁልፍ ተግባራት አንዱ መሆኑን የገለፁት እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፤ ባንኩ የተገበረው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ከ30 በመቶ በላይ ደርሶ የነበረውን የዋጋ ንረት በከፍተኛ መጠን ማውረድ መቻሉን ተናግረዋል።
በ2018 ህዳር ወር አጠቃላይ የዋጋ ንረት 10.9 በመቶ መውረዱንም ነው ያነሱት።
የዋጋ ንረትን በዚህ አመት ወደ ነጠላ አሀዝ ለማውረድ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካትም ባንኩ የሚተገብረውን ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
ብሔራዊ ባንክ የወለድ ምጣኔን በማስቀመጥ ኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ገንዘብ በዚህ የሚመራበትን አዲስ አሰራር በሪፎርሙ ተግባራዊ ማድረጉንም አንስተዋል።
በካፒታል ገበያ ስርዓት በባንኮች መካከል የገንዘብ ግብይት ከተጀመረ ወዲህ 1.1 ትሪሊዮን ብር ከገበያ ውስጥ መሰብሰብ መቻሉንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሌሎች ሀገራት አቻ ተቋማት ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርጉትን አዳዲስ አሰራሮችን በሪፎርሙ ተግባራዊ ስለማድረጉም ነው የገለፁት።
በቀጣይም ብሔራዊ ባንክ ቁልፍ ተግባሩ የሆነውን ዋጋ ማረጋጋት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
በጌታቸው ባልቻ
#Ebc #Ebcdotstream #Ethiopia #economy