Search

የኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ታሪካዊ እና ሁለገብ ግንኙነት በትብብር ላይ የተመሰረተ ነው - የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ

ሰኞ ጥቅምት 24, 2018 135

የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ሕብረት ኢንቨስትመንት ፎረም በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ከኢንቨስትመንት ፎረሙ ጎን ለጎን፣ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፣ በፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ኒኮላ ፎሪሲየር ጋር ገንቢ የሆነ የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
ውይይቱ የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ማጠናከር እና ፈረንሳይን በኢትዮጵያ የምታደርገውን ኢንቨስትመንት ማሳደግ ላይ ያተኮረ ነበር።
ሁለቱም ወገኖች የቆየውን አጋርነታቸውን እና ዘላቂና ሁሉን አቀፍ ዕድገትን ለማስቀጠል ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ውይይቱ የኢንዱስትሪ ልማት፣ ታዳሽ ኃይል፣ መሰረተ ልማት፣ የግብርና ምርቶች ማቀነባበር እና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ጨምሮ ሰፋ ያሉ የጋራ ልማቶች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተመላክቷል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ፣ ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ የልማት ሥራዎች እያደረገች ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን ማቅርባቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
ኢትዮጵያ ለችግሮች የማይበገር፣ ተወዳዳሪ እና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የጀመረችው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ያስመዘገበውን ውጤት ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
መንግስት ግልጽ በሆኑ ፖሊሲዎች እና ተቋማዊ ማሻሻያዎች የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ለማሻሻል እና የዓለም አቀፍ ተሳትፎን ለማሳደግ እያደረገ ያለውን የተጠናከረ ጥረት አብራርተዋል።
አቶ አሕመድ ሽዴ “ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ በትብብር ላይ የተመሰረተ ታሪካዊ እና ሁለገብ ግንኙነት አላቸው” ያሉት ሚኒስትሩ፤ ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማጠናከር ለምታከናውናቸው ተግባራት መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥም አመላክተዋል።
የፈረንሳይ የውጭ ንግድ ሚኒስቴር ተወካዮች ቀጣይነት ያላቸውን የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች አድንቀው፣ ፈረንሳይ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ እና የኢንቨስትመንት አጋርነቶችን በማሳደግ የንግድ ትስስሩን ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።
የፈረንሳይ ሚኒስትር በግንቦት 2026 ወደ ኢትዮጵያ በሚያደርጉት ይፋዊ ጉብኝት ወቅት ውይይቱን ለመቀጠል ሁለቱም ወገኖች ተስማምተዋል።
ስብሰባው በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ሕብረት መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ትብብር ለማጠናከር እና የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ለመደገፍ ጥራት ያለው ኢንቨስትመንት ለማሰባሰብ ያለመ ከፍተኛ ደረጃ ያለው መድረክ በሆነው የአውሮፓ ህብረት-ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኮንፈረንስ አውድ ውስጥ ተካሂዷል።
በጌትነት ተስፋማርያም