ኢትዮጵያ ላለፉት አምስት አሥርተ ዓመታት የስንዴ ዕርዳታ ስትቀበል የኖረች ሀገር ነበረች። ዛሬ ግን ያ የታሪክ ጠባሳ ተቀይሮ፣ ዓለምን በሚያስደንቅ ፍጥነት በስንዴ ራሷን ወደ መቻል ተሸጋግራለች።
ይህ ዝም ብሎ የተገኘ ለውጥ ሳይሆን በፖለቲካ ቁርጥኝነት ታቅዶ በጥበብ በመመራት በላብ የተገኘ ታላቅ ውጤት ነው።
የለውጡ ጅማሮና የፖለቲካ ቁርጠኝነት
ከጥቂት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ለስንዴ ግዢ ብቻ በዓመት ከ700 ሚሊዮን እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር ታወጣ ነበር። ይህንን የውጭ ምንዛሬ ጫና ለመቀነስና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ መንግሥት የቆላማ አካባቢዎችን የመስኖ ስንዴ ልማት እንደ ዋና ስትራቴጂ ነደፈ።
"በጥረት የማይቻል የለም" የሚል መንፈስን በማንገብ፣ የተበጣጠሱ መሬቶች በኩታ ገጠም አስተራረስ ምርታማ የሚሆኑበት ሰፊ ሥራ ተጀመረ።
የበጋ ስንዴ ተዓምር
የኢትዮጵያ ግብርና ከዝናብ ጥገኝነት ተላቅቆ ወደ መስኖ መሸጋገሩ ትልቁ ድል ነው። ቀደም ሲል ዝም ብለው የተተው ቆላማ አካባቢዎች ዛሬ ወደ ወርቃማ የስንዴ ማሳነት ተቀይረዋል።
ለአብነትም በአፋር፣ በሶማሌ እና ቦረና አካባቢዎች የሚታየው ለውጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመስኖ ስንዴ የሚለማበትን መሬት ከጥቂት ሺህ ሔክታሮች ወደ ሚሊዮኖች አሳድጎታል። ይህም በዓመት ሁለት እና ሦስት ጊዜ በማምረት የምርት መጠኑን በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጎታል።
ሜካናይዜሽን እና የቴክኖሎጂ ሽግግር
አርሶ አደሮች ማሳቸውን በኩታ ገጠም በማቀናጀታቸው ለእርሻ ሜካናይዜሽን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ እና የፀረ-ተባይ መድኃኒቶች በሰፊው ጥቅም ላይ ውለዋል።
እርሻው በትራክተር መታረሱ ምርታማነትን ከመጨመሩ ባሻገር፣ ምርትን በኮምባይነር መሰብሰቡ የምርት ብክነትን በመቀነስ የጥራት ደረጃውን ከፍ አድርጎታል።
ራስን ከመቻል ያለፈ የኤክስፖርት ጉዞ
ኢትዮጵያ አሁን ላይ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ስንዴን ሙሉ በሙሉ በራሷ ማምረት ችላለች። ራስን ከመቻል አልፋም ከሁለት ዓመታት በፊት በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴን ወደ ውጭ ሀገር መላክ (Export) ጀምራለች። ኬንያ፣ ጅቡቲ እና ሱዳን ከኢትዮጵያ ስንዴ የሚገዙ ቀዳሚ ሀገራት ሆነዋል። ይህም ሀገሪቱ በቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ በር ከፍቷል።
የዓለም አቀፍ ተቋማት ምስክርነት
የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አኪንውሚ አዴሲና (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ያመጣችውን ለውጥ "ለአፍሪካ አርአያ የሚሆን ሥራ" ሲሉ ደጋግመው አድንቀዋል። ኢትዮጵያ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ያስከተለውን የዓለም የምግብ ቀውስ በራሷ ጥረት መቋቋም መቻሏ ለብዙዎች አስገራሚ ሆኖባቸዋል።
የዛሬው መልዕክትና ቀጣዩ ተስፋ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የኢትዮጵያ የስንዴ ፕሮግራም ራስን የመቻል ጉዞ ግብ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ "በ2018 የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሩብ ዓመታት አጠቃላይ የስንዴ ምርት 126.69 ሚሊዮን ኩንታል ደርሷል። ይህም የመስኖ ስንዴ ምርትን ሳይጨምር ነው!"
ይህ ውጤት የሚያሳየው ኢትዮጵያ ከስንዴ ልመና ወጥታ የኢኮኖሚ ነፃነቷን እያረጋገጠች መሆኑን ነው። ይህ በግብርናው ዘርፍ የታየው ስኬት እንደ ቡና፣ የቅባት እህሎችና በኢንዱስትሪው ዘርፍም ሊደገም እንደሚችል በተግባር የታየበት ማሳያ ነው።
በለሚ ታደሰ