በቁርጠኝነት ከተሠራ ከተማ እና ሀገርን በደንብ መለወጥ እንደሚቻል አዲስ አበባ ማሳያ ናት ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባላት ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ ስኬት ለሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች አርአያ እንደሚሆንም አመራር አባላቱ ገልጸዋል።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት እንዲሁም የቤት ልማት እና አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ፥ በጉብኝቱ አዲስ አበባ የኢትዮጵያን ገጽታ ከፍ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችን እያከናወነች መሆኗን ተመልክተናል ብለዋል።
በተለይም የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷን የሚያጸኑ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን አይተናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ጉብኝቱ በአመራር ቁርጠኝነት እና በነቃ የሕዝብ ተሳትፎ ሀገር መለወጥ የሚያስችል መልካም ዕድል መኖሩን ያመላከተ ነው ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፥ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በአዲስ አበባ ያየናቸው የልማት ሥራዎች ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማማ ለማድረስ በትክክለኛው መስመር ላይ መሆናችንን አመላካች ናቸው ብለዋል።
አያይዘውም፥ የሀገሪቱን የልማት ትልሞች ከዳር በማድረስ ተጨማሪ ስኬቶችን ለማስመዝገብ ዝግጁ ነን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ መነቴ ሙንዲኖ በበኩላቸው፥ የአዲስ አበባ የልማት ስኬት ለሌሎች ከተሞች ከፍተኛ ልምድ እንደሚሆን ተናግረዋል።
አክለውም፥ ልማትን ቀጣይነት ባለው መልኩ እያረጋገጡ ለመሄድ ተግባራዊ እርምጃዎችን በላቀ ደረጃ የምንወስድበት ጊዜ ነው ብለዋል።
#ebcdotstream #ethiopia #prosperityparty #development #projects