Search

ኢትዮጵያ በዓመት 5 ቢሊዮን ዶላር ልታገኝበት የምትችለው እና ዓለም ከፋሽን እስከ ኮንስትራክሽን የሚጠቀምበት ተክል

ሰኞ ኅዳር 01, 2018 1214

በዚህ ዓለም ላይ ለግንባታ ከሚውሉ ግብዓቶች አንዱ ከሆነው ብረት በላይ ምን ጠንካራ ነገር ይኖራል? እስከአሁን ድረስ በግንባታው ዓለም ማጠንከሪያው ብረት ሆኖ ግዙፍ ግንባታዎች ጭምር ሲከናወኑበት ዘመናትን ተሻግሯል።

ታዲያ በዚህ ዘርፍ እንደጃፓን ያሉ በመሬት መንቀጥቀጥ የሚቸገሩ ሀገራት ከብረት ይልቅ ቀርከሃን የመምረጣቸው ምስጢር አስገራሚም ደግሞም ዕይታን የቀየረም ነው።

ከልጆች ዳይፐር እስከ ፋሽኑ ዓለም ተወዳጅ ልብሶች፣ ከጣፋጭ ምግቦች እስከ መድኃኒትነት ይዘት ያለው መጠጥ እንዲሁም ከቅንጡ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እስከ ውድ የዓለማችን ለስላሳ ጨርቆች የሚመረቱት ከቀርከሃ ነው ቢባል ለማመን የሚከብድ ቢመስልም እውነታው ግን ይህ ነው።

ደግሞም ወዲህ የሰው ልጅ የምድር ላይ ፍላጎቶቹ ብዙ ቢሆኑም የሚያስማሙት ነጥቦች ግን ከአምስት አይዘሉም። ለዚህም ነው መሰረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶቹ ምግብ፣ መጠለያ፣ ልብስ፣ ውሃ እና አንዳንዴ እንቅልፍ እና ሌሎች ጉዳዮችን በማካተት የሚያስቀምጡት።

እናም እነዚህን ፍላጎቶቹን ለማሟላት ከግለሰብ እስከ መንግሥታት በየዘርፉ ይጥራሉ። አንዳንዴ ታዲያ ተፈጥሮ አሟልታ ለሰው ልጅ ሰጥታለች የሚሉ ሞጋቾች ምክንያታቸው ብዙ ነው። የሰው ልጅ ከመሰረታዊ ፍላጎቶቹ ውስጥ በርካታውን ለመመለስ የሚያስችለው የተፈጥሮ ስጦታ ቀርክሃ ነው ቢባል ማን ያምናል? ግን እውነታው እንዲሁ ነው።

የሰው ልጅ የሚመገበው፣ የሚለብሰው እና መጠለያውንም የሚቀልስበት ቀርከሃ ታዲያ የተፈጥሮ ገጸ በረከት ነው ቢባል አያንስበትም።

ለመሆኑ እንዴት ነው ቀርክሃ ለሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች ውስጥ ሦስቱን ማሟላት የሚችለው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ምላሹም ቀላል እና አንድ ሁለት ተብሎ ሊነገር የሚችል ስለመሆኑ እንመለከታለን።

ከዚህ በፊት ግን ኢትዮጵያ በቀርከሃ ሃብቷ ከአፍሪካ አንደኛ እንደሆነች እንደውም 60 በመቶው የአፍሪካ ቀርከሃ መገኛ መሆኗን ጥናቶች ያመላክታሉ የሚለውን እውነታ ማስታውስ ያስፈልጋል።

ለዛውም ደግሞ የደጋ፣ የቆላ እና የውጭ ዝርያ ያላቸው በሚል የሚታወቁ ሲሆን 62 በመቶ የቆላ ቀርከሃ ዝርያ መገኛው በቢንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነው። 38 በመቶ የደጋ ቀርከሃ ዝርያ መገኛ ደግሞ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሲዳማ ክልሎች እንዲሁም በሀገሪቱ የደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ነው። ታዲያ ይህ ራትም ጉርስም ብሎም የኢኮኖሚ መደገፊያም የሆነ ተክል እንዲህ በኢትዮጵያ የሚገኝ ከሆነ ለምን አልተጠቀምንበትም ያስብላል።

እዚህ ላይ ታዲያ በዓለም ላይ ምግብም፣ ልብስም ሆነ መጠለያ ያደረጉት ሀገራት ያገኙት ጠቀሜታ እውነትም ይህ ተክል ተዓምረኛ ነው ቢባል ልኩ ይሆናል። ይህን ቁጭት በመረዳት ታዲያ እንደልብ የማይገኘውን የቀርከሃ ዘር በማባዛት በአረንጓዴ ዐሻራ በየዓመቱ በስፋት እየተተከለ ነው።

ይህን ተዓምረኛ ተክል ኢትዮጵያ እንዳላት ሃብት በአግባቡ ብትጠቀምበት በዓመት እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት እንደምትችል የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት (FAO) ጥናት ያመላክታል። ይህ ማለት ታዲያ ኢትዮጵያ 2017 ከጠቅላላ የወጭ ንግድ ካገኘችው 8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ጋር ሲነጻጸር ምን ማለት እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም። 

ዓለም ዘመናዊ የሆኑ የወለል ንጣፎች፣ ነዳጅ (ኢታኖል) ምግብ፣ መጠጥ፣ ሻይቅጠል፣  ውድ አልባሳት፣ አንሶላ፣  ባህላዊና ዘመናዊ መድኃኒቶች፣ የህጻናት ዳይፐር እና ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ምርቶችን በመስራት ጥቅሙን እየተቋደሰ ነው።

ታዲያ ይህን ሁሉ ነገር ነው ለመስራት የሚያገለግለውን  የቀርከሀ ተክል ከሚያመርቱ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር በዓለም ደግሞ የስምንተኛ ደረጃ ላይ መገኘቷን ለተመለከተ ብዙ የኋላ ቁጭቶችን የፈጥራል።

የዓለም የእርሻና ምግብ ድርጅት (FAO) ጥናት እንደሚያመላክተው ኢትዮጵያ  የቀርከሃ ተክልን ለማልማት የሚያስችል እስከ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት አላት።

ይህንን አቅም ተጠቅማ ምርቱን በዘመናዊ ኢንዱስትሪ ደረጃ መቀየር ብትችል  እና 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ብታለማ በየዓመቱ እስከ 5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚደርስ ገቢ እንዲሁም 1.3 ሚሊዮን ሰዎች የሥራ ዕድሎችን መፍጠር የሚያስችል እምቅ አቅም እንዳላት የዓለም የእርሻና ምግብ ድርጅት (FAO) ከጥቂት ዓመታት በፊት ያደረገው ጥናት ያመላክታል።

ዛሬ ላይ ሀገራት  ቀርከሀ የሚሰጠውን  ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በመገንዘብ ቀርከሀን በብዛት ከማልማት ባለፈ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የታገዙ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት ከቀርከሀ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ  ምርቶችን ማምረት የቻሉ በዓመት በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ችለዋል።

በእነዚህ ሀገራት ቀርከሀ በሰፊው ከሚታወቅበት ጥቅም ባሻገር፣ በዘመናዊ ኢንዱስትሪዎች ቀርቀሃን ዘመናዊ ልብስ ድረስ በመቀየር በፋሽኑ ዓለም ተወዳጅ የሆኑ አልባሳትን ማምረት ተችሏል።

በብዙ ሂደት አልፈው ከቀርከሀ የሚመረቱ ጨርቃ ጨርቆች  ከጥጥ በበለጠ ልስላሴና እርጥበትን የመምጠጥ ችሎታ ያላቸው በመሆኑ የህጻናት ዳይፐሮችን በዋጋቸው ውድ የሆኑ ካልሲዎችን  ሸሚዝ እና አንሶላዎችን ለመስራት በጥቅም ላይ ይውላሉ።

በተፈጥሮ ፀረ-ባክቴሪያ ባህርይ ያላቸው ከቀርከሀ የሚሰሩ አልባሳት  በዓለም ገበያ ተፈላጊነት ያላቸው ከመሆኑም በላይ በዋጋ ረገድም በውድ የሚሸጡ ምርቶች ናቸው።

ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው የቀርከሀ ዛፍ በህንጻ ግንባታ ዘርፍ  እንደጃፓን ባሉ ሀገራት ብረትን ተክቶ መለስተኛ ህንጻዎችን ለመገንባት በጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኝ ጭምር ነው። ለረጃጅም ህንጻዎች የሚያገለግሉ ጠንካራ ፓኔሎችን፣ የወለል ንጣፎችን እና የቤት ዕቃዎችን ለማምረት ይጠቅማል።

ከዚህም ባለፈ ቀርከሃ ከፍተኛ መጠን ያለው ሴሉሎስ (Cellulose) የተባለ ንጥረ ነገር በውስጡ የያዘ በመሆኑ በኬሚካላዊ እና ባዮሎጂካዊ ሂደቶችን ውስጥ እንዲያልፍ በማድረግ ወደ ኤታኖል ሊለወጥ ይችላል።  ይህም ከቀርከሀ የተገኘ ባዮኤታኖል ከነዳጅ ጋር በመቀላቀል ለተሽከርካሪዎች በጥቅም ላይ ማዋል ተችሏል።

በቻይና እና በአንዳንድ የሩቅ ምስራቅ ሀገራት ከብዙ ሺህ ዘመናት ጀምሮ ቀርከሀን ለምግብ እና አንዳንድ ባህላዊ መድሀኒቶችን ለመስራት ሲገለገሉበት የቆየ ነው። በቻይናና በአንዳንድ የኤዥያ ሀገራት እንዲሁም በአፍሪካዊቷ ታንዛንያ ከቀርከሀ የአልኮል መጠጦችን ማምረት የተለመደም ነው።

በብዙ ሀገራት ተወዳጅ የሆነውን ከቀርከሀ ሥር የሚዘጋጅ ምግብን ጨምሮ ሻይ ቅጠል እና አልኮል የሌለው  ጭማቂ ለመስራት የሚያገለግል ተክል ነው።

በተለይ እንደቻይና ባሉ ሀገራት የቀርከሀ ተክልን በዘመናዊ ኢንደስትሪዎች በማቀነባበር የሚመረት የሻይ ቅጠል  ለጤና ከሚሰጠው ጥቅም አንጻር በአውሮፓ ገበያዎች በሰፊው ተቀባይነት ማግኘት ችሏል።

የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተም ለማገዶነት የሚውሉ የከሰል እና ባዮፊውል ምርቶችን ከቀርከሀ በመስራት የደን መመናመንን ለመቀነስ በሰፊው ጥቅም ላይ ሲውል የቆየ ነው። ከሌሎች ዛፎች 35 በመቶ የበለጠ ኦክስጅን በመስጠት የአየር ንብረት ለውጥን በመቀየር ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።

ይሁን እንጂ ለዚህ ታላቅ ጥቅም መስጠት ለሚችል  የቀርከሀ ሀብት ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘቱ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ሳትሆን ቆይታለች።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ምርቱን ለማሳደግና ወደ ውጭ በመላክ ገቢ ለማግኘት እየተሞከረ ያለ ቢሆንም የቀርከሀ ምርቶችን ወደተለያዩ ነገሮች በመቀየር በዓመት በቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ከቻሉ ሀገራት አንጻር ሲታይ ለቀርከሀ ተክል የተሰጠው ትኩረት አሁንም አናሳ ነው።

በዓለም ቀዳሚ የሆነችው ቻይና ባሳለፈው 2024 6.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ችላለች።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ይህንን በፍጥነት የሚያድግ እምቅ ሀብት የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ የቆየች ሲሆን ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጥናት ተድርጎ በቀርከሀ ኢንዱስትሪ ለሚሰማሩ እና በመስራት ላይ ለሚገኙ ድርጀቶች ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ 1.4 ሚሊዮን ሄክታር ላይ የለማ ቀርከሃ እንዳላት የሚገመት ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት 250 ሺህ ዶላር ገቢ ማግኘት መጀመሩ እና በአረንጓዴ ዐሻራ ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶት እየተተከለ መሆኑ እውነትም የዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት (FAO) ጥናት እንደሚያመላክተው በአጭር ጊዜ ከፍተኛውን የውጭ ንግድ የምታስመዘግብበት እንደሚሆን የጥሩ ማሳያ ነው።

በዋሲሁን ተስፋዬ