የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በመተባበር፤ ባልተፈቀዱ የውጭ የሐዋላ ገንዘብ ማስተላለፍ ሥራዎች ላይ በተሰማሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ የተቀናጀ አርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታወቀ።
አነዚህ አርምጃዎች የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሥርዓት በመጠቀም ድንበር ዘለል የገንዘብ ማስተላለፍ ተግባራትን በሚፈጽሙ ደላሎችና ገንዘብ አቅራቢዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድን ያካትታሉ ብሏል፡፡
ይህ አርምጃ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ሥርዓትን ተአማኒነት ለመጠበቅና የውጭ ምንዛሪ ፍስት በሕጋዊ፣ ግልጽና መደበኛ በሆኑ መንገዶች መከናወኑን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ገልጿል።
በመሠረቱ፤ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሮችን ለመፈጸም መደበኛ የፋይናንስ ሥርዓትን መጠቀም የውጭ ምንዛሪ ገበያን ተአማኒነት የሚያኮሰስና የሀገሪቱን የገንዘብ ሥርዓት አደጋ ላይ የሚጥል አካሄድ ነው ብሏል ባንኩ፡፡
በአንጻሩ፤ አነዚህ የማስተካከያ አርምጃዎች ሕገ ወጥ የሐዋላ ዝውውርን ለመከላከል የሚደረግ ጥረት አካል መሆናቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያሳውቃል። ባንኩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሥርዓት ላልተገባ ዓላማ ለመጠቀም የሚፈልጉ አካላትን በመለየት ተገቢ አርምጃ መውሰዱን ይቀጥላል ሲል ገልጿል፡፡
አንዲሁም፤ ባንኩ የውጭ ሐዋላ ፍሰት መደበኛ አካፄድን ተከትሎ አንዲፈጸም የሚረዱ አርምጃዎችን ለማጠናከርና በባንኮችና ሕጋዊ ፈቃድ ባላቸው የገንዘብ አስተላላፊዎች አማካይነት በቂና ቀጣይነት ያለው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት መኖሩን ለማረጋገጥ ተግቶ እንደሚሰራም አመላክቷል።
እነዚህ የባንኩ ጥረቶች የሐዋላ ፍሰት ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ግልጽ በሆነ መንገድ አንዲፈጸም ለማድረግና የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መረጋጋትና የልማት ግቦች ለማሳካት የታለሙ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
በመሆኑም፣ ሕዝቡ ሕጋዊ የውጭ ሐዋላ አገልግሎት አቅራቢዎችን ለይቶ ማወቅ ይችል ዘንድ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕግን ተከትለው በውጭ ምንዛሬ ገበያ አንዲሳተፉ የተፈቀደላቸውን የሐዋላ አስተላለፊ ድርጅቶችን ስም ዝርዝር በድረ ገጽ አድራሻ ማለትም በ https://nbe.gov.et/mta/ አስቀምጧል፡፡
በመጨረሻም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕጋዊ የገንዘብ ማስተላለፊያ ዘዴዎችን አጠቃቀም የሚያበረታታና ሕዝቡ በፋይናንስ ሥርዓት ላይ ያለውን ተዓማኒነት የሚያጠናክር ደህንነቱ የተጠበቀና ጠንካራ/ምቹ የፋይናንስ ከባቢ ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆኑን ያሳውቃል ሲል ገልጿል።