Search

የተፈቀደላቸው የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችን አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

ረቡዕ ኅዳር 03, 2018 210

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያ የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት እንዲሰጡ የተፈቀደላቸውን የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችን ስም ዝርዝር ለሕዝቡ ይፋ አድርጓል።
በዚሁ መሠረት፣ ቀደም ሲል የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት እንዳይሰጥ ታግዶ የነበረው እና ዋና መሥሪያ ቤቱ በአሜሪካ ቪርጂኒያ ግዛት በፎልስ ቸርች የሚገኘው ራማዳ ፔይ (ካህ) በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ አጠቃላይ ግምገማ ከተካሄደ በኋላ በሕጋዊ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ስም ዝርዝር ውስጥ ዳግም እንዲካተት ተደርጓል።
ከዚህ ውሳኔ ላይ ሊደረስ የቻለው በሀገሪቱ ሕግ እና ደንብ መሠረት በድርጅቱ ላይ አስፈላጊው የቁጥጥር እና የክትትል ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ ነው።
ስለሆነም፣ ባሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ አገልግሎት እንዳይሰጡ ታግደው የሚገኙ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በሙሉ የሀገሪቱ ሕግና ደንብ የሚጠይቀውን መስፈርት ለማሟላት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያበረታታል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዓላማ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በግልጽነት እና ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ብቻ እንዲሠሩ ድጋፍ ማድረግ ነው።
በመሆኑም፣ ውጭ ሀገር የሚኖሩ ሰዎች ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ በሚያስተላልፉበት በማንኛውም ወቅት ሕጋዊ እና ግልጽ የሆነ አካሄድ መከተላቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።
ሕጋዊ ፈቃድ በተሰጣቸው የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በኩል ገንዘብ መላክ ገንዘቡ ደኅንነቱ ተጠብቆ እና ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን እና አሸባሪነትን በገንዘብ መደገፍን የሚጻረረውን አሠራር ተከትሎ ወደ ተቀባዩ እንዲደርስ ያደርጋል።
ሕዝቡ ፈቃድ የተሰጣቸው የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችን ለይቶ ለማወቅ ይችል ዘንድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሕጋዊ ድርጅቶችን ስም ዝርዝር በድረ-ገጽ https://nbe.gov.et/mta/ ላይ አስፍሯል።
በመጨረሻም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕጋዊ የሐዋላ አገልግሎትን ለማበረታታት እና የፋይናንስ ዘርፍን ጤናማ ዕድገት ለመደገፍ የሚረዳ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ግልጽ እና ቀልጣፋ የፋይናንስ ምኅዳር እንዲኖር ተግቶ መሥራቱን እንደሚቀጥል አስገንዝቧል።