ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ 4ኛውን ዓመታዊ የማዕድን እና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ (MINTEX Ethiopia 2025) በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በይፋ ከፍተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት “ኢትዮጵያ ምድሯም ልጆቿም ሀብታሞች ናቸው እስክንባል ድረስ ለአፍታም አንቆምም” ብለዋል።
“ኢትዮጵያ ምድሯ ባለ ሦስት ድርብ ሀብት የያዘ ነው፤ የከርሰ ምድር ሀብቶች፣ የገጸ ምድር ሀብቶችን እና ልዩ የአየር ንብረትን ታድላለች” ሲሉም አክለዋል።
ይህን ድልብ ሀብት ከነበረበት የመረሳት አባዜ በማላቀቅ፤ ለሁለንተናዊ ብልፅግና ማሳኪያ ለመጠቀምና የኢትዮጵያን ዕድገት ለማረጋገጥ ጉዞ ጀምረናልም ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
መንግሥት የሰጠው ልዩ ትኩረትና የወሰዳቸው እርምጃዎች ለዘርፉ መነቃቃት እና ተስፋን በማምጣት፤ በማዕድን ኢንቨስትመንትና በወጪ ንግድ ከፍተኛ እመርታን እንደፈጠሩም ነው ያነሱት።
ዓለም አቀፍ ኤክስፖው ባለድርሻ አካላትን፣ ባለሀብቶችን፣ የቴክኖሎጂ አምራቾችን እና ምሁራንን በማሰባሰብ፤ ያሉንን መልካም ዕድሎች የምናሳይበት እና ተግዳሮቶችን በቅንጅት የምንፈታበት ወሳኝ መድረክ ነው ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።