በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በየዓመቱ በአማካኝ 24 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እየገቡ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ተናግረዋል፡፡
ከለውጡ በፊት በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞንና የደብረ ብርሃን ከተማ በአጠቃላይ በማምረት ላይ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ቁጥር 18 ብቻ እንደነበር የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡
በአሁን ወቅት በደብረ ብርሃን ከተማ ብቻ የመካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ቁጥር 105 መድረሱን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በቀሩት የዞኑ አካባቢዎች ደግሞ ተጨማሪ 87 ኢንዱስትሪዎች በማምረት ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡
ቁጥሩ እንደሚያመለክተው በአካባቢው በአማካይ በየዓመቱ 24 የሚሆኑ መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት እየገቡ መሆኑን ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም በዓመት ይህን ያህል ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸው በክልሉ የኢንዱስትሪ አብዮት እየተቀጣጠለ መምጣቱን ያመላክታል ብለዋል፡፡
የኢንዱስትሪ መስፋፋት ከኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ባሻገር ከሀገር ሉዓላዊነት እና ክብር ጋር ተጣምሮ ሚታይ የኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን ማብሰሪያ ነው ሲሉ ነው የገለጹት፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ለጠንካራ መንግሥት ግንባታ፣ ገጠርን ከከተማ ጋር በማስተሳሰር ፍትሃዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ለማስቻል የሚያግዝ እና በሌሎችም ዘርፎች ላይ በጎ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ መሆኑንም ሚኒስትሩ አመላክተዋል፡፡
መንግሥትም ይህንን በማመን የፖሊሲ እና የአደረጃጀት፣ የግብዓት፣ የመሰረተ ልማት፣ የፋይናንስ እንዲሁም የተቀናጀ አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ሥራዎችን በኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ