ዛሬ በይፋ ተመርቆ ሥራ የጀመረው የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የላቀ የሕክምና ማዕከል ዓለም አቀፍ ጥራት ደረጃ በጠበቀ መልኩ ተገንብቶ ዘመኑን የዋጀ የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥን የሚያሟላ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
በውጪ ሀገራት ንፁህ እና ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያ የተሟላላቸው የሕክምና ማእከላትን ስናይ “መቼ ይሆን በሀገሬ ይህንን የመሰለ ለባለሙያው፣ ለታካሚው እንዲሁም ለአስታማሚው ጭምር የተመቸ ዘመናዊ የጤና ማዕከል የሚኖረው?” ለሚለው ቀና ቁጭት ምላሽ የሰጠ ነውም ብለዋል።
ይህ የላቀ የሕክምና ማዕከል የተለያዩ አገልግሎቶች የተካተቱበት ሲሆን፦
• የተኝቶ ሕክምና ህሙማን ክፍሎች (IPD)
• የህፃናት እና የአዋቂዎች ፅኑ ህሙማን ክፍሎች (ICU)
• የኦክስጅን ማምረቻ ፕላንት
• የቪአይ ፒ አልጋዎች
• የኦፒዲ ክፍሎች
• የኦፕራሲዮን ክፍሎች(OR) እና የማገገሚያ ክፍሎች እንዲሁም
• የድንገተኛ ክፍል አልጋዎች
• በየሕክምናው አይነትና በየወለሉ ፋርማሲ እና የመድሃኒት ስቶር
• ላቦራቶሪ
• የአስተዳደር ቢሮዎች
• የማብሰያ ክፍሎች፣ ዋና ካፊቴሪያ፣ በየወለሉ ለሚገለግሉ ባለሙያዎች የሚሆኑ ካፊቴሪያዎች
• የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎችን ከውብ ምድረ ግቢ ጋር ማካተቱን ጠቁመዋል።
ከንቲባዋ ይህን ለማኅበረሰቡ ፋይዳው እጅግ የላቀ የጤና ማዕከል ለአገልግሎት እንዲበቃ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያበረከቱ ተቋማት፣ አመራሮች እና ባለሙያዎችን በተገልጋዩ ኅብረተሰብ እንዲሁም በራሳቸው እና በከተማ አስተዳደሩ ስም አመስግነዋል።
በማዕከሉ የሚገኙ ባለሙያዎች፣ ለሕሙማን የሚሰጡትን አገልግሎት የሚያቀልላቸው የላቀ የሕክምና ማዕከል እንኳን አገኛችሁ በማለት፣ በአግባቡ እንዲጠቀሙበት እና ከምንጊዜውም በላይ ሙያዊ ሥነ-ምግባር እና ርኅራኄ እንዳይለያቸው አደራ ብለዋል።