Search

ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ የሆነው የምርታማነት ሥራ

ቅዳሜ ኅዳር 06, 2018 146

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር መንግሥት መጽሐፍ የሀገር ውስጥ አቅሞችን በጋራ በማሰባሰብ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የተሻለ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያመላክታል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ጀማል አደም (ዶ/ር) ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን ለማስፈን አንድ ሀገር መሰረታዊ ነገሮችን በራሷ ማምረት እንዳለባት ገልፀዋል።
ምግብ እና የመሳሰሉትን መሰረታዊ ነገሮችን በራስ ማሟላት የማይችል ኢኮኖሚ በሌሎች ላይ ጥገኛ ይሆናል ያሉት ባለሙያው፤ እንዲህ ያለው ጥገኛ ኢኮኖሚ የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት ከማሳጣቱም በላይ፣ የራስን ሀብት የመጠቀም ሥልጣንን እንደሚያስነጥቅም አብራርተዋል።
ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት የአንድን ሀገር ስጋቶች የመከላከል አቅምን በማጠናከር የዕድገት ጉዞን እንደሚያፋጥንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እያደረገች የምትገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አንዱ ትኩረቱ የወጪ ንግድ ሚዛኑን በማስጠበቅ መሰረታዊ የሚባሉ ምርቶችን ማምረት መሆኑን ጀማል አደም (ዶ/ር) ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አቶ አሰፋ ሱሞሮ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአህጉር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፋዊ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ላይ ንቁ ተሳታፊ ልትሆን እንደሚገባ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር እንደመሆኗ ያሏትን ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ መጠቀም እንደሚገባት አመላክተዋል።
በአፍሪካ ያለውን የንግድ ትስስር በመጠቀምም ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሟን ማስጠበቅ እንደሚጠበቅባት ገልፀው፤ ይህም ከመደመር ፍልስፍና አንፃር፣ የሀገር ውስጥ አቅምን በማጎልበት ትብብርን ላይ የተመሰረተ ተጠቃሚነትን ያጎላል ሲሉ አስረድተዋል።
 
በንፍታሌም እንግዳወርቅ