በኮምቦልቻ ለዘመናዊ አገልገሎት እና ለሰው ተኮር ተግባራት የተሰጠው ትኩረት የሚደነቅ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በዛሬው ዕለት የኮምቦልቻ ሪጆፖሊታን ከተማ አስተዳደር የዲጂታል አገልግሎት እና የዘመናዊ የሥራ ቦታ እድሳት እና ሰው ተኮር ተግባራትን ተመልክተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ተከትሎ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባጋሩት ጽሑፍ፥ የኮምቦልቻ ሪጆፖሊታን ከተማ አስተዳደር ህንጻ የስማርት ሲቲ እሴቶችን ባሟላ መልኩ መታደሱን ገልጸዋል።
ህንጻው ዲጅታል አሠራርን ለመተግበር በሚያስችል መልኩ መደራጀቱ አገልግሎትን ለማዘመን አጋዥ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
ሌላው በከተማዋ የተመለከትነው በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ለሚገኙ ነዋሪዎች ተገንብተው ለነዋሪዎች የተላለፉ መኖሪያ ቤቶችን ነው።
የከተማ አስተዳደሩ ባለሀብቶችን እና ህብረተሰቡን በማስተባበር ባስገነባቸው ሁለት የመኖሪያ ብሎኮች ለአቅመ ደካሞች እና አረጋውያን ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶችን ማስረከቡንም ጠቅሰዋል።
አያይዘውም፥ “በኮምቦልቻ የጎበኘናቸው የዲጂታል የከተማ አገልግሎት ፕሮጀክት እና ሰው ተኮር ተግባራት በከተሞቻችን እየተገበርናቸው ያሉ የአካታች ልማት ማሳያዎች ናቸው” ብለዋል።