Search

የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ጠባቂነትን አስወግዶ በሀሳብ ሀብት መፍጠር እንደሚቻል አሳይቷል - የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር

ሰኞ ኅዳር 08, 2018 150

የኢትዮጵያ የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ጠባቂነትን አስወግዶ በሀሳብ ሀብት መፍጠር እንደሚቻል ያሳየ ተቋም መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

በኢትዮጵያ ባለፉት 7 ዓመታት ኢንተርፕረነርሺፕን የመንግሥት መለያ ማድረግ የሚያስችሉ ተቋማት እና ሕጎች መተግበራቸውን ጠቅሰዋል።

የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት "በጋራ እንገንባ" በሚል መሪ ሀሳብ ተከፍቷል።

ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ስሟን ከፍ ያደረጉ፣ አንቱ የተባሉ ምስጉን እና ታታሪ ኢንተርፕረነሮችን ስትፈጥር ቆይታለች።

ይሁን እንጂ ሀገሪቱ ኢንተርፕረነርሺፕን የመንግሥቷ መለያ ማድረግ የሚያስችሉ ተቋማትን የገነባችው፣ ሕጎችን ያወጣችው እና የኢንተርፕረነርሺፕን ምህዳር ተቋማዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ያደረገችው ባለፉት 7 ዓመታት ነው።

የመደመር መንግሥት ኢንተርፕረነር ስለመሆን አስፈላጊነት እና ኢትዮጵያ እንዴት ኢንተርፕረነር እንደምትሆን በግልጽ አስቀምጧልም ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሀሰን ሁሴን (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ የኢንተርፕረነርሺፕ ሁነቶችን በማዘጋጀት ብራዚልን በመቅደም ከዓለም 1ኛ ሆናለች ብለዋል።

ኢንተርፕረነሮች የፈጠራ መፍትሔዎችን ወደ መሬት የሚቀይሩ፣ ምኞትን የሚያሳኩ፣ አይቻልምን ችለው የሚያሳዩ ፈር ቀዳጅ ባለራዕዮች እና ከዋኞች ናቸው ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የሚወሰን ሳይሆን ድንበር ተሻጋሪ ሥራ ጀምረናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የመጨረሻ ግባችን አይበገሬ ማህበረሰብ፣ ዜጋ እና ሀገር መገንባት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

#EBCdotstream #Ethiopia #entrepreneurship #GEW2025