መንግሥት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ እና የሀገር ውስጥ ምርትን በበቂ ሁኔታ ለማሳደግ ተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል።
የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለኢትዮጵያ ፍላጎት በቂ ምርት የማቅረብ አቅም እና ጸጋ እንዳለው በመገንዘብ የተቀረጸው የተኪ ምርት ስትራቴጂ፣ ኢትዮጵያ ለገቢ ምርቶች የምታወጣውን ወጪ በመቀነስ በቢሊዮን ዶላር የሚገመት የውጭ ምንዛሬ እንድታድን ማስቻሉን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በአብነት ጠቅሷል።
እንደ ሀገር ያጋጠሙ የኢኮኖሚ ስብራቶችን ለመጠገን እና የኢንዱስትሪ ዘርፉን ችግሮች ለመፍታት በተወሰደው ቁርጠኛ እርምጃ፣ ዘርፉ በ2017 በጀት ዓመት የ13 በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ያስቻለ አንጸባራቂ ወጤት ማየት ተችሏል ብሏል።
እንደ ሀገር የዘርፉ መነቃቃት፣ ክልሎች ያላቸውን ጸጋ በመግለጥ እና ለኢንቨስትመንት ምቹ ዓውድ በመፍጠር የኢትዮጵያ ብልፅግና የሚገለጥባቸው አገራዊ አቅም እንዲሆኑ ማድረጉንም ነው አገልግሎቱ በማኅበራዊ ትስስር ገፁ ባጋራው መረጃ የገለጸው።
እንደ አገልግሎቱ መረጃ፥ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብቻ ከ271 በላይ ፕሮጀክቶች የሚገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 131 የሚሆኑት በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩ ናቸው።

በክልሉ ጉዙፍ የሚባለው ፕሮጀክት በምስራቅ ጉራጌ ዞን እየተገነባ የሚገኘው ቡል ኤለፋንት ፋይበር ቦርድ ማኑፋክቸሪንግ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ እንደ ኤም ዲ ኤፍ፣ ኤች ዲ ኤፍ እና ፋይቨር ውድ ያሉ ተኪ ምርቶችን ሙሉ በሙሉ በራስ ዐቅም በማምረት ኢትዮጵያን ከውጪ ምንዛሬ ወጪ የሚታደግ ነው።
በቻይናያውያን ባለሀብቶች እየተገነባ የሚገኘው እና አፈፃፀሙ ከ50 በመቶ በላይ የደረሰው ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ ከ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገበ ሲሆን፤ በግንባታው ሂደት ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማማሳለጥ ከጅምሩ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
#ebcdotstream #ethiopia #manufacturing #importsubstitution