Search

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 6 ተጨማሪ ኤርባስ አውሮፕላኖችን አዘዘ

ማክሰኞ ኅዳር 09, 2018 140

በዱባይ አየር ትርኢት ላይ አየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ 6 ተጨማሪ ኤርባስ A350-900 አውርፕላኖችን ለመግዛት ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ የአየር መንገድ ብራንዶች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያዘዛቸው ተጨማሪ ኤርባስ አውሮፕላኖች በአፍሪካ ትልቁ የኤርባስ ደንበኛ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

ስምምነቱ የተፈረመው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው እና በኤርባስ የንግድ አውሮፕላኖች ሽያጭ ኃላፊ ቤኖይት ደ ሴንት ኤክሱፔሪ መካከል ነው።

አቶ መስፍን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀዳሚ የኤርባስ ደንበኛ የሚያደርገውን የግዢ ስምምነት በመፈረሙ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አየር መንገዱ የእነዚህ ዘመናዊ አውሮፕላኖች ባለቤት መሆኑ ዓለም አቀፍ ተደራሽነቱን ለማስፋት እና ለደንበኞቹ የሚሰጠውን አገልግሎት የበለጠ ምቹ ለማድረግ እንደሚያግዘውም ጠቅሰዋል።

የኤርባስ ሽያጭ ኃላፊው በበኩላቸው፤ ኤርባስ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ያለውን ደንበኝነት በማጠናከሩ ደስተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አውፕላኖቹ በአፍሪካ የአቪዬሽን የላቀ ደረጃ ላይ ለደረሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቅልጥፍና እና ሁለገብነት እንደሚጨምሩ ተናግረዋል።

ኤርባስ ከሌሎች አውሮፕላኖች ጋር ሲነጻጸር የነዳጅ ፍጆታው 25 በመቶ የቀነሰ መሆኑን የጠቆሙት የሽያጭ ኃላፊው፣ ይህም ለአየር መንገዱ ተጨማሪ ዕድል እንደሚያመጣ ገልጸዋል፡፡

ኤርባስ ከውስጣዊ ምቾቱ ባሻገር የነዳጅ አጠቃቀሙ ከቀዳሚው ትውልድ አውሮፕላኖች ጋር ሲነፃፀር የካርቦን ልቀትን በመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ይጠቀሳል።

በለሚ ታደሰ

#EBC #EBCdotstream #FlyEthiopian #EthiopianAirlines #Airbus #DubaiAirshow2025