Search

ዛሬን በቅጡ በመሥራት ለሀገር የሚተርፍ ወረት የማበራከት ዕሳቤ

እሑድ ኅዳር 21, 2018 119

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ “በመደመር መንግስት እይታ፣ የዘርፎች እመርታ“ በሚል ርዕስ ለብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በሰጡት ስልጠና፣ ከኋላቀርነት ወደ ስልጣኔ ስለሚያሸጋግሩ ሀሳቦች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፤ ከኋላ ቀርነት ለመውጣት፣ የድህነት አዙሪትን ለመስበር፣ የሀብት እጥረትን ቀርፎ ወረት ለማበራከት እንዲሁም ትላንትን ከነገ ጋር ለማስተሳሰር "የዛሬን ድልድይ" መገንባት በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
"ዛሬ ላይ ያልተገነባ ድልድይ ወደ ነገ አያሸጋግርም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዛሬን በቅጡ በመሥራት እና ዞር ብሎ ሁኔታዎችን በመገምገም መፍጠር፣ መፍጠን እና ሲያስፈልግም መዝለል (Leapfrog) እንደሚቻል አንስተዋል፡፡
በአስተሳሰብ አዙሪት ውስጥ ሆነን ‘ትላንት፣ ትላንት’ ስንል ዛሬ እና ነገ ይረሳሉ፤ ‘ነገ፣ ነገ’ ሲባል ደግሞ የዛሬ ሥራ ይዘገያል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተመሳሳይ መልኩ ውስጣዊ ጉዳይ ላይ ብቻ ስናተኩር ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ሊያመልጡ ይችላሉ ሲሉ አስረድተዋል።
በመሆኑም ሁሌም በተከታይነት እና በችግር አዙሪት ውስጥ የምንሽከረከር እንዳንሆን፤ ዓለምንና ራሳችንን በሚገባ የምንገነዘብ፣ ዛሬን በቅጡ የምንሠራ እና ያለፈውንም ዞር ብለን የምናይ መሆን አለብን ብለዋል።
 
በሀይማኖት ከበደ
All reactions:
62