ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር መንግሥት እሳቤ ዙሪያ ለብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በሰጡት ሥልጠና የኢትዮጵያን ሥልጣኔ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ቅድመ አክሱም እና ከአክሱም በኋላ በሚል በሁለት በመክፈል አብራርተዋል።
ከቅድመ አክሱም ሥልጣኔዎች ውስጥ ፑንት፣ ዳማት እና ኩሽ ሥልጣኔዎች ይጠቀሳሉ።
የፑንት ሥልጣኔ ግማሽ የሚያህል ኢትዮጵያን ይዞ ዋና ትኩረቱ ቀይ ባህርን የሚቆጣጠር ነው።
ፑንት ሥልጣኔ ውድቀትን ተከትሎ የመጣው የኩሽ ሥልጣኔ የቀይ ባህርን በስፋት ይዞ ወደ ኋላ እስከ ሱዳን ድረስ ይሰፋ እንደነበር አመላክተዋል።
የኩሽ ሥልጣኔ ወድቆ የዳማት ሥልጣኔ ሲመጣም ማጠንጠኛው ቀይ ባህርን እና ዓባይን መቆጣጠር ነበር ብለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ መንግሥታት እና ሥልጣኔዎች ዋናው ማጠንጠኛ እና መሠረታቸው ቀይ ባህርን እና ዓባይን መቆጣጠር እንደሆነ ታሪካዊ ዳራን ተመሥርተው አብራርተዋል።
የአክሱም ሥረወ-መንግሥት ሲመጣ ወደ የመን እና ወደ ደቡባዊ ሳዑዲ እና ሕንድ ድረስ የሚዘረጋ ሰፋ ያለ ተፅዕኖ የነበረው እና በወቅቱ ከነበሩ አራቱ ኃያላን መንግሥታት እንደ አንድ የሚወሰድ መንግሥት እንደነበር ነው ያስታወሱት።
በዓለም ላይ የነበሩ ሥልጣኔዎች ከድንጋይ ጋር የሚያያዙ እንደሆኑ ጠቅሰው በኢትዮጵያም የአክሱም፣ የሃ፣ ላሊበላ እና ሶፍ ዑመር የዚሁ ማሳያ እንደሆኑ አመላክተዋል።
ይህ ሆኖ ሳለ በግብጽ ያለው ከድንጋይ የተሠራው ፒራሚድ ብዙ ፊልሞች የተሠሩለት እና የሥልጣኔ መገለጫ ሆኖ ስሙ ሲጠቀስ በእኛ ስንፍና ምክንያት የኛዎቹ ብዙ ያልተነገረላቸው መሆኑ የሚያስቆጭ እንደሆነ ብለዋል።
ከአክሱም ሥልጣኔ በኋላ የነበሩ የዛጉዌ፣ የጎንደር፣ የሐረር፣ የጅማ፣ የሸዋ፣ የካፋ፣ የወላይታ፣ የዳውሮ እና ሌሎች ሥልጣኔዎች እንደሚጠቀሱ አንሥተዋል።
ዳውሮዎች የዛሬ 400 ዓመታት ገደማ ሐላላ ኬላን ሲሠሩ 47/48 ዓመት እንደፈጀባቸው፤ በወቅቱ አንድ ቤተሰብ ለ7 ዓመታት በሥራው ላይ የመቆየት እና የመሥራት ግዴታ እንደነበረበት ጠቅሰዋል።
በዚህም የአንድ ዓመት ልጅ ጥሎ ወደ ሥራው የተሰማራ ሰው ግዴታውን ጨርሶ ሲመለስ ልጁ የ8 ዓመት ሆኖ ይጠብቀው ነበር ማለት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ መንገድ በትውልድ ቅብብሎሽ ሐላላ ኬላን እንደገነቡ አውስተዋል።

ማሽቆልቆል እንዴት መጣ?
በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የነበሩ ሥልጣኔዎች ከሌሎች የዓለም ሀገራት ሥልጣኔዎች ጋር የተቀራረበ ባሕርይ እያለቸው የኛዎቹ ለምን አሽቆለቆሉ? ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
እንደ እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ ለኢትዮጵያ ሥልጣኔዎች ማሽቆልቆል ውስጣዊም ውጫዊም ምክንያቶች አሉ።
ከውስጣዊ ምክንያቶችም የመንግሥታት መዳከም፣ የሕዝብ ብዛት እና የአቅርቦት መሳሳት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል። የሕዝብ ብዛት እና አቅርቦት አብረው የማያድጉ ከሆነ ግጭት መፍጠሩ፣ ግጭት ደግሞ መዳከምን መፍጠሩ አይቀርም።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጣኔ የመጣባቸውን ዘመናት እና በኋላም ውድቀት የመጣባቸው ዘመናትን ከመኪና ጎማ ጋር በማመሳሰል ነው የገለጹት።
የመኪና ጎማ ከአንድ ቦታ ተነሥቶ የሚፈለገው ቦታ ለመድረስ አራት ሁነኛ ነገሮች ይጠበቁበታል። እነዚህም የጎማዎቹ እኩል መጠን መሆን፣ በእኩል ሰዓት አንድ ላይ መሽከርከር መቻል፣ አራቱም በአንድ አቅጣጫ መሄድ እና በእኩል ፍጥነት መጓዝ መቻል ናቸው። እነዚህ አራቱ ሁኔታዎች በእያንዳንዱ ሁኔታ ውስጥ አንዱ የተዛነፈ ከሆነ ወደ ሚፈለገው ከመድረስ አስቸጋሪ መሆኑን በዝርዝር አብራርተዋል።
ይህንንም ከሀገር ሥልጣኔ ጋር አያይዘው ሲያብራሩ፣ የኢትዮጵያን ኅልውና ለማረጋገጥ፣ ብልፅግናዋን መሥራት እና መሠረት መጣል የምንፈልግ ከሆነ በእኩል ልንሮጥ ይጠበቅብናል ሲሉ አስገንዝበዋል
አንድ ሀገር ከሌሎች ኋላ ቀረ የሚባለው ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ መስፈሪያዎች ዝቅ ካለ፤ በኢኮኖሚ እና በቴክኖሎጂ ከፍ ካሉ ሀገራት ዝቅ ብሎ ሲገኝ ነው።
የዕድገት መገታት፣ የፍጥነት መጓተት፣ የፖለቲካ አዙሪት፣ የኢኮኖሚ ስብራት የመሳሰሉ ሁኔታዎች የኋላቀርነት መገለጫዎች ናቸው።

የኋላቀርነት መንሥኤዎች ደግሞ ተቋማዊ ውድቀት፣ ባህላዊ ዝቅጠት እና ኢኮኖሚያዊ ልሽቀት መሆናቸውን ጠቁመው ምክንያቶቹንም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከሥልጣኔ ጋር በተያያዘ ያሳለፈችውን ሁኔታ ሲገልጹም፣ በዘመን መካከል ቀደምት ሆና ማሳለፏን፣ ተቸንክራ መቅረቷን፣ በሆነ አዙሪት ውስጥ መግባቷን፣ በጣም መዘግየቷን፣ መንሸራቷን እና ኋላ መቅረቷን ጠቁመዋል።
በጊዜ እና በዘመን መቀደም የሚያስከትለው ጣጣ መዘጋት፣ መዘግየት መንሸራተት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እየዘገየን በዘመን ስንቀደም ብዙ ጉዳዮች በእኛ ላይ እየተዘጉ ዘመን ሲለወጥ እኛ እዛው ቆመን እንደምንቀር ጠቁመዋል።
ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ የሺህ ዓመታት ሂደት ውስጥ የነበረ ችግር መሆኑን ነው የተናገሩት።
በዚህ ሁሉ መሐል ታዲያ የኢትዮጵያን መዘግየት፣ ማሽቆልቆል፣ መድከም እና መደህየት ብንናገርም ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ እያነሰች እና እየሰፋች፣ እየወደቀች እየተነሣች እዚህ መድረሷ ተስፋ እንዳለ አመላካች ነው ብለዋል።
ከእነ ችግሩም ቢሆን አሁንም ሀገር መሆናችን፣ ስለ ሀገር ለማውራት መሰባሰብ መቻላችን ተመልሰን ለመነሣት እና ወደ ፊት የበለጠ ለማደግ ትልቅ ተስፋ መሆኑን ነው የገለጹት።
ስለዚህ ያለፉ ታሪኮቻችንን በመቆዘም ብቻ ሳይሆን በተስፋ ማየትም አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።
በዮናስ በድሉ
#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #medemer #PMAbiy