Search

ትርፍ ያለው ከሰላም ብቻ ነው - በአማራ ክልል የምሥራቅ ጎጃም ዞን ነዋሪዎች

ሰኞ ኅዳር 22, 2018 99

የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በምሥራቅ ጎጃም ዞን የአዋበል ወረዳ እና ሉማሜ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም፣ ከግጭት እና ከጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለም፤ ትርፍ ያለው ከሰላም ብቻ ነው፤ ሰላምን በአንድነት ማጽናት ይገባናል ሲሉም ተናግረዋል።
ተወያዮቹም፤ ወደ ኋላ ላለመቅረት ሰላምን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመመለስ እና የትምህርት ስብራቱን መጠገን ይገባል ብለዋል።
 
ሰላም በእጃችን ስንይዘው ቀላል ነው፤ ስናጣው ግን ዋጋ ከፍለንበታል ያሉት ነዋሪዎቹ፤ የውስጥ ችግሮችን በሰላማዊ አማራጮች እና በውይይት መፍታት እንደሚገባም አንስተዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት በቅንጅት መሥራት፣ ያልጠራውን መዋቅር ማጥራት እና ቁርጠኛ መኾን ይገባል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።
 
በተያያዘ ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በደብረ ማርቆስ ከተማ እየተገነባ የሚገኘውን ዘመናዊ ሆስፒታል፣ የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) እያስገነባው የሚገኘውን ሕንጻ እና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ የከተማዋን እድገት እና የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በደብረ ማርቆስ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው ሆስፒታል እስከ ሚያዝያ 2018 ዓ.ም መጨረሻ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመው፣ የአማራ ልማት ማኅበር(አልማ) ሕንጻም በዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።