የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከአንድ ዘርፍ ጥገኝነት ተላቆ በብዝሃ ዘርፍ አቅም ላይ የተገነባ የልማት ስትራቴጂን እንዲከተል ተደርጓል።
ከ2010 ዓ.ም በፊት የነበረው ግብርና መር ፖሊሲ ለኢኮኖሚው እድገት ማነቆ ሆኖ እንደነበር ያነሱት በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ናቸው።
ከለውጡ ወዲህ ግን የመደመርን የትብብር ሞዴል በመከተል፤ በግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ ኮሪደር ልማት እና በተለያዩ መስኮች ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ገልጸዋል።
አዲሱ አሰራር የተለየዩ ዘርፎች ራሳቸውን ችለው ለሀገር ኢኮኖሚ አመርቂ ውጤት እንዲያመጡ ማስቻሉን ተናግረዋል።
የዲቨሎፕመንት እና ኢኮኖሚክስ ተመራማሪው ገመቺስ መርሻ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት የነበሩ የኢኮኖሚ ሥርዓቶች ከውጭ የተኮረጁና የሀገርን ተጨባጭ ሁኔታ ያላገናዘቡ በመሆናቸው ኢኮኖሚው ላይ የተሻለ ለውጥ ማምጣት እንዳልተቻለ አመላክተዋል።
የመደመር መንግሥት ከዚህ በመማር፤ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ የተረዳ እና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ትግበራን መከተሉን አንስተዋል።
ይህም ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ለውጥ በማምጣት ተስፋ ሰጪ ውጤት ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡
በሜሮን ንብረት