ዛሬ ማለዳ የከተማ አስተዳደራችን በሰጠው ልዩ ትኩረት እና ቁርጠኝነት ለ30 ሺህ የከተማችን ወጣቶች እና ሴቶች አዲስ የሥራ ዕድል ፈጥረናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ አበባ የማድረግ ሥራ የነዋሪዎቿንም ኑሮ እና አኗኗር በመለወጥ ጭምር ነው ሲሉ ጠቁመዋል።
ዛሬ ወደ ሥራ ያስገባናቸው እነዚህ አዲስ ሥራ ጀማሪዎች ቀደም ሲል በተለያዩ መድረኮች ስንወያይ የሥራ ዕድል ጥያቄ የነበራቸው ወጣቶችና ሴቶች ናቸው ብለዋል።
የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎቹ በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው በከተማ ግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በንግድ፣ በአገልግሎትና በሌሎችም አዋጭ ዘርፎች ላይ በልዩ ሁኔታ በማሰማራት ዛሬ ሥራ አስጀምረናል ሲሉም ገልጸዋል።
ይህ በከተማችን በስፋት እየተተገበረ ያለው የአንድ ጀምበር የስራ ዕድል ፈጠራ ንቅናቄ በቀጣይነት በልዩ ትኩረት እየተደገፈ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ በቀጣይም በላባቸው ፍሬ የሚኖሩ፣ ሥራ ፈጣሪ፣ ታታሪ ዜጎችን በሁሉም መስክ መደገፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በሥራ ዓለም የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ በማድረግ የጀመርነውን የብልጽግና ጉዞ በሙሉ ቁርጠኝነት እውን ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት በከተማችን ይበልጥ ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል ብለዋል።
የሥራ ዕድሉ የተፈጠረላችሁ ወጣቶች እና ሴቶች፣ አስተዳደራችን ለእናንተ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል ያደርግላችኋል ሲሉም ከንቲባዋ አስታውቀው፤ በተፈጠረው ዕድል በአግባቡ በመጠቀም እና ጠንክሮ በመሥራት የራሳቸውን፣ የከተማዋን ታሪክ የሚቀይሩ ውጤታማ ዜጎች መሆን እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።