Search

የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ ለኢኮኖሚ እድገቱ ሚናውን የበለጠ እንዲወጣ እየተሰራ ነው፡- ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

ረቡዕ ኅዳር 24, 2018 115

በአማራ ክልል የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ ለኢኮኖሚ እድገቱ ሚናውን የበለጠ እንዲወጣ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መሥተዳድሩ በባሕር ዳር ከተማ በልዩ ልዩ የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎቶች ለመሰማራት ቦታ ተረክበው በተለያየ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ባለሃብቶች ጋር እየተወያዩ ነው።
ውይይቱ በባሕርዳር ከተማ በአገልግሎት ዘርፍ የተሠማሩ አልሚዎች ለግንባታ እና ሥራ ለመጀመር ያሉባቸው ችግሮች ላይ በመወያየት፣ የባለሃብቶችን የልማት ተግዳሮቶች በጋራ በመፍታት በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ለማስገባት ያለመ ስለመሆኑ ተገልጿል።
በውይይቱም የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ በሀገር በቀል ብዝኀ ኢኮኖሚ ዘርፍ ትኩረት የተሰጠው ስለመሆኑ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል፡፡
ዘርፉ ለኢኮኖሚ እድገቱ ያለውን አበርክቶ ለመወጣት የ25 ዓመት ፍኖተ ካርታ እና የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ ስለመሆኑም አንስተዋል።
ባለሐብቶች ለልማት የወሰዱትን መሬት ያለልማት ከ20 ዓመትና በላይ አጥረውና በጅምር ግንባታ ላይ የቆሙ ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡ አሳስበዋል።
መሬት ከወሰዱ በኋላ ሕንጻ ቢገነቡም፣ አገልግሎት መስጠት ያልጀመሩ የአገልግሎት ዘርፉ ከሚፈጥረው የኢኮኖሚ አቅም እና የሥራ እድል አንፃር በየስምሪት ዘርፋቸው አገልግሎት እንዲጀምሩም ማሳሰቢያ የተሰጠበትም ነው።
በውይይቱ ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እና ሌሎችም የከተማ አሥተዳደሩ መሪዎች እና በክልሉ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ተገኝተዋል።
 
በራሔል ፍሬው