የመደመር መንግሥት ዋነኛ ግብ የሆነው ታሪክን በመሥራት ውጤትን በተግባር የመግለጥ እሳቤ፤ በግብርናው ዘርፍም ላይ ለውጥ በማምጣት ላይ ይገኛል፡፡
ግብርናን በአዲስ እይታ በመምራት ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡
የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት እና በግብርና መዋቅራዊ ሽግግር የምርት ስብጥርን ለማብዛት በተሰራው ሥራ፤ ከሰብል በተጨማሪ የአትክልት እና ፍራፍሬ የመሬት ሽፋን እና ምርትም ከፍተኛ ዕድገት ሊያስመዘግብ ችሏል፡፡
በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የግብርና እና ውኃ ሃብት ምህንድስና መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ሲሳይ ደመቁ (ዶ/ር)፤ 73 በመቶ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ዜጎች መተዳደሪያ ግብርና መሆኑን በኢቢሲ አዲስ ቀን መሰናዶ ላይ ተናግረዋል፡፡
ስለሆነም ግብርናውን ማዘመን እና ማሳደግ ከተቻለ፣ 73 በመቶ የሚሆኑ ዜጎችን ኢኮኖሚ ማሻሻል እና የኑሮ ደረጃቸውን ከፍ ማድረግ እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ተመራማሪ የሆኑት አቶ ገዛኸኝ በሬቻ በበኩላቸው፤ ምርታማነትን ለማሳደግ አንደኛው መንገድ የግብዓት አጠቃቀም መሆኑን አንስተዋል፡፡
ለአምራቹ ዘመናዊ እና የተሻሻለ ዘር በማቅረብ እንዲሁም በማዳበሪያ አጠቃቀም ላይ የባለሙያ እገዛ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዘመናት ግብርናው በዓመት አንዴ ማምረት ላይ ብቻ ትኩረቱን አድርጎ ሲሰራበት መቆየቱን የጠቆሙት ተመራማሪው፤ አሁን ዓመቱን ሙሉ ማምረት በመቻሉ ለውጦች እየተስተዋሉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ