የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር (AFRAA) 57ኛ አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በአራት ዘርፎች አሸናፊ ሆኗል።
ማህበሩ በአንጎላ ሉዋንዳ ባዘጋጀው ዓመታዊ የእውቅና መድረክ ላይ ነው ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ሽልማቶቹን ያበረከተው።
በዚህም አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ስራዎች ትርፋማነት የ2024 ምርጥ አየር መንገድ እውቅናን ሲያገኝ፤ አፍሪካን በአየር ትራንስፖርት በማገናኘት የላቀ አገልግሎት በመስጠትም ማሸነፍ ችሏል፡፡
አየር መንገዱ ለአፍሪካ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ እድገት ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ፤ የላቀ አገልግሎት በመስጠት ዘርፍም አሸንፏል።
እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ ነፃ የአየር ትራንስፖርት እውን ለማድረግ ለያዘው ፕሮጀክት የላቀ አስተዋጽኦ በማድረጉም አየር መንገዱ ተሸላሚ መሆን ችሏል።
በአፍሪካ ከ60 በላይ በዓለም ከ145 በላይ መዳረሻዎች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ አፍሪካን በአየር ትራንስፖርት በመገናኘት የአንበሳውን ድርሻ ይዟል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያገኘው እውቅና የፓን አፍሪካን እሴቶች መጠናከር የሰጠውን ትኩረት ከማሳየቱም በላይ የተቋሙ ሰራተኞች ቁርጠኝነትና ትጋት ውጤት መሆኑን የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መሥፍን ጣሰው ገልፀዋል።
አየር መንገዱ ለቀጠናዊ ትስስርና እንዲሁም ለዘርፉ እድገት እያደረገ ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል።
በላሉ ኢታላ
#Ebc #Ebcdotstream #EthiopianAirlines #Africa #AFRAA