Search

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት መካከል የዘላቂ ሰላም ስምምነት ተፈረመ

ሓሙስ ኅዳር 25, 2018 238

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል የዘላቂ ሰላም ስምምነት ተፈርሟል፡፡
ስምምነቱን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅትን (አፋሕድ) በመወከል ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ ተፈራርመዋል።
ውይይቱ እና ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት እና በኢጋድ አደራዳሪነት ሲካሄድ ነው የቆየው።
 
ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋ ከበደ በአስተላለፉት መልዕክት፣ ዛሬ ለክልላችን ሕዝብ የመጀመሪያው ትልቅ የሰላም ኩነት የተካሄደበት ቀን ነው ብለዋል።
ከግጭት አሸናፊም ተሸናፊም የለም፣ ከሰላም ሁሉም ያተርፋል፣ ስምምነቱ ለሰላም ወዳድ ሕዝባችን ትልቅ እፎይታን ይሰጣል ነው ያሉት፡፡
የሕዝብና የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ለመጡ ወንድሞቻችን እንደ መንግስት አድናቆትና ክብር አለኝ ብለዋል፡፡
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅትን (አፋሕድ) በመወከል ስምምነቱን የተፈራረሙት ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ በበኩላቸው፣ ማንኛውም ግጭት በመጨረሻ የሚፈታው በውይይትና በድርድር ነው ብለዋል።
ችግሮችና የሀሳብ ልዩነትን በንግግር መፍታት ፖለቲካዊ ሽንፈት ሳይሆን ጥበብና ብልጠት መሆኑን ገልጸው፣ ችግሮችን ለመፍታት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ማበር ተገቢ አለመሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር አምባሳደር ሰልማ ማሊካ አዳዲ በበኩላቸው፣ ስምምነቱ የሀገሪቱን ቀጣይ መዳረሻ የሚያቃና ነው ብለዋል።
 
በወንደሰን አፈወርቅ