Search

ትሩፋታቸው ለትውልድ የሚተርፉት ግዙፍ ፕሮጀክቶች

ቅዳሜ ኅዳር 27, 2018 58

የኢኮኖሚ አቅምን የሚያጎለብቱ እና ለትውልድ የሚተርፉ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በመገንባት ላይ ይገኛሉ።
በተለያዩ ዘርፎች የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የወደፊት ብሩህ ተስፋ የሚያመላክቱ ናቸው የሚሉት በከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የመሰረተ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት አቶ የትምጌታ አስራት ናቸው።
ሚኒስትር ዴኤታው ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ አሁን ላይ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርጉ፣ የብልፅግና ጉዞን የሚያፋጥኑ፣ ከዛሬ አልፈው ለነገ ትውልድ የሚተርፉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ባህል መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
ቀደም ባሉ ጊዜያት የሚጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ባለመጠናቀቁ ሀገሪቱ ማግኘት ያለባትን ሀብት ሳታገኝ መቅረቷን አስታውሰው፤ የፕሮጀክት መጓተት ሀብት እንዲባክን ከማድረጉም ባለፈ የመልካም አስተዳደር ጥያቄን ሲያስነሳ መቆየቱንም ነው የገለጹት፡፡
የመደመር መንግሥት በፕሮጀክቶች ግንባታ ሂደት ላይ ሲነሱ የነበሩ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት በወሰደው እርምጃ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ ማድረግ ችሏል ሲሉ ጠቁመዋል።
ለአብነትም እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ፣ የቱሪዝም መዳረሻ ልማቶች፣ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች፣ የከተማ እና የገጠር የኮሪደር ልማት ሥራዎች እንዲሁም ግዙፍ የተለያዩ ልማቶች የመደመር መንግሥት ፕሮጀክቶችን መጨረስ እንደሚችል ማሳያ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ መምህር የሆኑት ብርሃኑ ደኑ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የመደመር መንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ የሚያደርገው የክትትል እና የቁጥጥር ሥራ ፕሮጀክቶቹ በጥራት እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ግንባታቸው እንዲጠናቀቅ ማስቻሉንም አመላክተዋል።
ግዙፍ ፕሮጀክቶቹም ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር የቻሉ እና ኢኮኖሚው ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ክፍተት እንደነበር ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ግን ያ አመለካከት እየተቀየረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
በሜሮን ንብረት