ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት የአባልነት ድርድሯን ባጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ በብርቱ ጥረትና ተቋማዊ ቅንጅት እየሰራች ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አዘጋጅነት "ኢትዮጵያን በንግድ በማስተሳሰር ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር" በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መሥራችና ግንባር ቀደም ተዋናይ ብትሆንም ለዓለም አቀፍ የንግድ ውሕደት ተቋማትና አሰራሮች ባይተዋር ሆና ቆይታለች ብለዋል፡፡
ከለውጡ ማግስት ወዲህ ግን የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የመሆን ሕልሟን እውን ለማድረግ ባደረገችው ጽናት የተሞላበት ጉዞ የድርድሩ ሂደት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡
ምንም እንኳን ጥረቱ ሁለት አስርት ዓመታትን የተሻገረ ቢሆንም፣ ባለፉት ሰባት ወራት ውስጥ በተካሂዱት 5ኛው እና 6ኛው የሥራ ቡድን ስብሰባዎች የተመዘገቡ ውጤቶች፣ የመፈጸም ውስጣዊ አቅማችንን በጉልህ አሳይተዋል ብለዋል፡፡
በተለይም በ6ኛው የሥራ ቡድን ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ የእስካሁኑ የሥራ ቡድን ስብሰባ ሪፖርት “ረቂቅ የሥራ ቡድን ሪፖርት” በመደረጉ፣ ሂደቱን አንድ ርምጃ ከፍ አድርጎታል፤ ይሄም የባለ ብዙ ወገን የድርድር ምዕራፍ መቋጫ ላይ መድረሳችንን ያሳያል ሲሉ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በተከተለችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የሪፎርም ስራዎች አያሌ ተግባራት መከናወናቸውን በማንሳትም ስራዎቹ በዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ያላትን ተሰሚነት እና ድርሻ ከፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
እነዚህና ሌሎችም የተሠሩ ሥራዎች፣ ኢትዮጵያ የድርጅቱን አባልነት ለማሳካት በተግባር የተደገፈ አስተማማኝ ቁመና ላይ እንደምትገኝ ማረጋገጫ ናቸውም ብለዋል፡፡
በአሸናፊ እንዳለ
#Ebc #Ebcdotstream #Ethiopia #WTO