የመደመር መንግሥት ለኢንዱስትሪ መስፋፋት እና ማደግ የተለየ ትኩረት ሰጥቷል። ለዘርፉ ማንሰራራት ምቹ መደላድል መፍጠር የሚያስችሉ የሪፎርም ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጻፉት “የመደመር መንግሥት” መጽሐፍ፥ የመደመር መንግሥት ኢንዱስትሪውን የሚደግፈው ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር ከሉዓላዊነት፣ ራስን ከመቻል፣ ማንም ላይ ካለመድደገፍ እና ከሀገራዊ ክብር አንጻር ስለመሆኑ ተጠቅሷል።
ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኃይሉ የተራ፥ የመደመር መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪው ትልቅ ቦታ መስጠቱን ገልጸዋል።

በተለይ ከሁለት ዓመታት ወዲህ በዘርፉ ተከታታይነት ያለው ሪፎርም በመደረጉ፤ አምራች ኢንዱስትሪው በማንሰራራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘርፉ ከጥገኝነት መላቀቂያ ወሳኝ የልማት ዘርፎች ተርታ መመደቡ በራሱ የመደመር መንግሥት እመርታ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው ብለዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚውን ማሻሻያ በአብነት የጠቀሱት አቶ ኃይሉ፤ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ገልጸዋል።
በሲዳማ ክልል በሚገኘው የይርጋለም አግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጥቂት የነበረው የአልሚ ባለሃብቶች ቁጥር ዛሬ ላይ 29 በመድረሱ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ ማደጉ ተመላክቷል።
አዳዲስ አልሚ ባለሃብቶችን ለመሳብ በተካሄዱ የኢንቨስትመንት ማስተዋወቂያ ፎረሞች ቻይናን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት የአብረን እንሥራ ጥያቄ እየመጣ እንደሚገኝም አቶ ኃይሉ አንሥተዋል።
ከአምራች አርሶ እና አርብቶ አደሩ ሥራ እስከሚፈጠርለት ዜጋ የበርካቶችን ሕይወት የሚነካው የኢንዱስትሪው ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ ጉልህ ድርሻ አለው።
በሲሳይ ደበበ
#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #industry #medemer