Search

ኢትዮ ቴሌኮምና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምርቶችን በዘመን ገበያ ለማቅረብ ተስማሙ

ዓርብ ታኅሣሥ 10, 2018 47

ኢትዮ ቴሌኮም ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚመረቱና የኤክስፖርት ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን በዘመን ገበያ አማካኝነት ለሀገር ውስጥ ሸማቾች ለማቅረብ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን ያደረጉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍስሐ ይታገሱ (ዶ/ር) ናቸው።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚመረቱ የተለያዩ ምርቶችን ዲጂታል ሥርዓትን በመጠቀም ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚቀርቡበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስችል የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍስሐ ይታገሱ (ዶ/ር) በፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ተናግረዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ አምራቾችን የዲጂታል ክህሎት አቅም በመገንባት፣ ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅና የገበያ ትስስር በመፍጠር አጠቃላይ የንግድ ሥነ ምኅዳሩን ወደ ዘመናዊና ተወዳዳሪ ደረጃ በማሸጋገር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
ስምምነቱ በሀገር ውስጥ በከፍተኛ የጥራት ደረጃ የሚመረቱ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳትን፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶችን፣ የአግሮ-ፕሮሰሲንግ ውጤቶችን፣ ኤሌክትሮኒክስና የቴክኖሎጂ ምርቶችን፣ መድኃኒትና የሕክምና ግብዓቶችን፣ የኬሚካልና የግንባታ ግብዓቶችን እንዲሁም ሌሎች የማኑፋክቸሪንግ ምርቶችን በዘመን ገበያ ለማቅረብ ያስችላል ተብሏል።
 
በኤዶምያስ ንጉሴ