Search

ውጤታማው የብዝኃ ኢኮኖሚ ምሕዳር

ዓርብ ታኅሣሥ 10, 2018 31

ኅብረብሔራዊት ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት በግብርና ላይ ያተኮረ የኢኮኖሚ ሥርዓት ስትከተል ቆይታለች። ይሁን እንጂ ዘርፉ ዘመናዊ ባለመሆኑና ተገቢው ትኩረት ባለማግኘቱ፣ ውጤቱ ከእጅ ወደ አፍ በዘለለ ሀገራዊ ብልጽግናን ማምጣት ሳይችል ቀርቷል።
በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ለዘመናት ለስንዴ ዕርዳታና ልመና እጇን ስትዘረጋ ኖራለች።
የመደመር መንግሥት ብዝኃ የኢኮኖሚ ምሕዳር መዘርጋቱን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃት እየታየ ይገኛል።
የአመራር ልኅቀት ባለሙያ የሆኑት አቶ ይመስገን መሳፍንት ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በኢትዮጵያ ከግብርና ባሻገር የተጀመረው የብዝኃ ኢኮኖሚ ሥርዓት የኢትዮጵያን አቅም በማሳደግ ረገድ ትልቅ ለውጥ እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት ስትከተለው የነበረውን ግብርና መር ኢንዱስትሪ ላይ የተገደበ የኢኮኖሚ አቅጣጫ በመቀየር፤ በቱሪዝም፣ በማዕድን፣ በቴክኖሎጂና በግብርና እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም የግብርና ዘርፉ እንዲዘምን በመደረጉ፣ ኢትዮጵያ በስንዴና መሰል ምርቶች ራሷን ችላ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሏን ባለሙያው አስረድተዋል።
ነገን አልሞ እየሠራ ያለው የመደመር መንግሥት፣ ቀደም ሲል አይነኬ ተብለው የሚታሰቡ ጉዳዮችን በማንሳት ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ እየሠራ መሆኑን አመላክተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሺዮሎጂ እና የሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት የኋላእሸት ሙሉነህ በበኩላቸው፤ በቅርቡ የተጀመሩት የማዳበሪያ ፋብሪካ እና የመስኖ ግድብ ግንባታዎችን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን መፃዒ ዕድል የሚወስኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከምኞት የተሻገሩ ተጨባጭ ውጤቶችም ኢትዮጵያን በመለወጥ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ የልማት ሥራዎቹ የተሻለ ውጤት እንዲያስገኙ የተጠናከረ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
ብዝኃ ኢኮኖሚን በማስፋፋትም ውጤታማ ሥራ ለማከናወን የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን መደገፍ እና ለውጤታማነታቸውም መትጋት እንደሚገባም ገልጸዋል።
 
በሜሮን ንብረት