Search

በ11 የተሽከርካሪ ጎማ ሱቆች፣ ያለደረሰኝ ሲሸጡ የተገኙ 15 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ቅዳሜ ታኅሣሥ 11, 2018 57

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በመዲናዋ በተለያዩ አካባቢዎች የተሽከርካሪ ጎማ በሚሸጡ የንግድ ድርጅቶች ላይ ዛሬ ባካሄደው ድንገተኛ ኦፕሬሽን፣ ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ የተገኙ 15 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አሳውቋል።

ቢሮው ለኢቢሲ የላከው መግለጫ እንደሚያመለክተው፥ ለረጅም ጊዜ በተካሄደ ጥናት ላይ ተመስርቶ መርካቶን ጨምሮ በ12 የተመረጡ የከተማዋ የጎማ መሸጫ ቦታዎች ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በቅንጅት በተከናወነው ኦፕሬሽን፤ የመንግሥትን ግብር ለመሰወር ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ የተያዙ 15 የመኪና ጎማ ነጋዴዎች በሕግ ቁጥጥር ስር ውለዋል።

ከግብር ሕግ ጋር በተፃረረ መልኩ ምርትን ያለደረሰኝ ሽጠው መንግሥትን ጥቅም ለማሳጣት በመሞከር የተጠረጠሩት ግለሰቦቹ ጉዳያቸው በፖሊስ ተይዞ ለፍርድ እንደሚቀርቡ የየገለጸው ቢሮው፤ ኦፕሬሽኑ በቀጣይ ቀናት በሌሎችም ዘርፎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

የንግዱ ማህበረሰብ ግብይቶችን በደረሰኝ ብቻ እንዲፈፅም፤ ህብረተሰቡም በ7075 ነፃ የስልክ መስመር በመጠቀም መሰል ወንጀሎችን እንዲያጋልጥ ተጠይቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በታክስ አስተዳደር አዋጅ 983/2008 ዓ.ም መሠረት በመዲናዋ የሚፈፀሙ ሕገ-ወጥ ግብይቶችን የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ነው።