የኢትዮጵያ አጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፍ ጤናማ፣ ትርፋማና የተረጋጋ ነው ሲሉ የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት የሚለካበት አራት ነጥቦች መኖራቸውን ያነሱት የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፤ ባንኮች ያላቸውን ካፒታል፣ የተበላሸ ብድር፣ ትርፋማነታቸው እንዲሁም በቂ የገንዘብ ክምችታቸውን በማየት ልኬት ይደረጋል ብለዋል፡፡
የፋይናንስ ዘርፉ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው አነስተኛ ምጣኔ በላይ እያስመዘገበ ነው ያሉት የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ፤ ዘርፉ ውጤታማ ሒደት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በባንኮች ያለው የካፒታል ክምችት 8 በመቶ እንዲሆን ብሔራዊ ባንክ የሚጠብቅ ሲሆን፣ ሆኖም ግን የካፒታል ክምችታቸው ከ18 በመቶ ላይ መድረሱንም ተናግረዋል፡፡
ብሔራዊ ባንክ በአወጣው መመሪያ ባንኮች 15 በመቶ የጥሬ ገንዘብ ክምችት እንዲኖራቸው ነው ቢደነግግም፣ በአሁኑ ጊዜ ባንኮች ያላቸው የጥሬ ገንዘብ ክምችት ከ31 በመቶ በላይ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህ ማለት ግን አንዳንድ ባንኮች ችግር የለባቸውም አሊያም ድጋፍ አይፈልጉም ማለት እንዳልሆነ ያነሱት የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ፤ አማካዩ ሲታይ ያሉበት ደረጃ በጣም ጥሩ የሚባል ነው ብለዋል፡፡
ስለሆነም ባንኮች ባለፈው የበጀት ዓመት ያገኙት ትርፍ እና እስካሁን ባለው ሒደት ውጤታማ ናቸው ያሉት እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፤ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው እስካሁን ያላገኘውን ከፍተኛ ትርፍ ነው እያስመዘገበ ያለው ብለዋል፡፡
የዲጂታል ባንኪንግ ዘርፍ በሚገርም ፍጥነት ማደጉንና በዚህም 18.5 ትሪሊዮን የገንዘብ ዝውውር መካሄዱን አንስተዋል፡፡
ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች በበኩላቸው ከ400 ቢሊዮን በላይ የገንዘብ ክምችት አድርገዋል፤ ሆኖም ግን ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች በመስኮት ደረጃ አገልግሎቱን እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በባንኮች የሚስተዋለው የተበላሸ ብድር ምጣኔ በጥሩ ደረጃ ላይ የሚቀመጥና ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠውን ደረጃ ያሟላ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በመሀመድ ፊጣሞ