Search

ለአካባቢ ተስማሚ መሆናቸው የተነገረላቸው ‘ዱዱ’ ባለሶስት እግር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሥራ ገቡ

ሓሙስ ታኅሣሥ 16, 2018 389

የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማዘመን እና የአየር ብክለትን ለመግታት ታስበው የተመረቱት "ዱዱ" ዘመናዊ ባለሶስት እግር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በዛሬው ዕለት በይፋ ተመርቀው ወደ ሥራ ገብተዋል።

በዱዱ ቪኢክል ማኑፋክቸሪንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር በተለያየ ሞዴል የተመረቱት ባለሶስት እግር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ የተሳፋሪ እና የእቃ ማጓጓዣ ናቸው። ተሽከርካሪዎቹ አንዴ ቻርጅ ተደርገው እስከ 150 ኪሎ ሜትር መሄድ ይችላሉ ተብሏል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የዘርፉ ተዋንያን እንደገለጹት፥ ዛሬ ሥራ የጀመሩት ተሽከርካሪዎች የሀገሪቱን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በተግባር ለማገዝ ትልቅ ፋይዳ አላቸው።

የዱዱ ቪኢክል ማኑፋክቸሪንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚስተር ዛኦ ቲያን፥ "ዱዱ" ባለሶስት እግር  ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ በመሆናቸው፣ በየቀኑ ለነዳጅ የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ ለመቀነስ ያስችላሉ ብለዋል።

ይህም ለአሽከርካሪዎች እና ለተሳፋሪዎች ትልቅ የኢኮኖሚ እፎይታን ይዞ መምጣቱን ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው የገለጹት።

ለጥገና አነስተኛ ወጪ ብቻ የሚጠይቁት እነዚህ ተሽከርካሪዎች፤ ለአሽከርካሪዎች የተሻለ ትርፍ፣ ለተሳፋሪዎች ደግሞ ምቾት እና ደህንነቱ የተጠበቀ ጉዞን ያረጋግጣሉ ተብሏል።

ተሽከርካሪዎቹ ምንም ዓይነት የአየር እና የድምጽ ብክለት የማይፈጥሩ በመሆናቸው ለአካባቢ ንጽህና እና ለነዋሪዎች ጤና ተመራጭ መሆናቸው ተመላክቷል።

ተሽከርካሪዎቹ በሀገር ውስጥ ባለ የመገጣጠሚያ ፋብሪካ የሚመረቱ በመሆናቸው ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠራቸው ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲካሄድ እንደሚረዱ ተጠቁሟል።

በወይንሸት ደጀኔ

#EBC #ebcdotstream #AddisAbaba #dodo #electricvehicles