የብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ምሰሶዎች ላይ የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና አስተባባሪ አቶ ዮዳሄ አርአያሥላሴ ገልጸዋል።
አቶ ዮዳሄ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን በተመለከተ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የስትራቴጂው መሠረታዊ ምሰሶዎች አካታችነት፣ የአገልግሎት ተደራሽነት እና መተማመንን መፍጠር መሆናቸውን ጠቁመዋል።
አካታችነት ሲባል ለሁሉም የዲጂታል ኢኮኖሚ ተሳታፊነትን ማረጋገጥ ሲሆን፤ የጎጆ ኢንዱስትሪ፣ ጥቃቅን እና አነስተኛ ቢዝነሶች ንግዳቸውን ለማሳደግ፣ አርሶ አደሩ ምርት እና ምርታማነቱን ለመጨመር የብድር አቅርቦት ማስፋት ሲቻል እንደሆነ አብራርተዋል።
የአገልግሎት ተደራሽነት ደግሞ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ ሁሉም ዜጋ በቅርብ ርቀት እንዲያገኝ ማስቻል ነው።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ዜጎች ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለሚሠሩት ሥራ ወይም ግብይት ከመንግሥት ጋር መስተጋብር እንዲፈጥሩ ማድረግና በዚህም መተማመን መፍጠር ሦስተኛው ምሰሶ እንደሆነ ነው የገለጹት።
ብሔራዊ መታወቂያን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ የግብርና ግብዓቶችን፣ ግብርን፣ የብድር አቅርቦትን ለማግኘት፣ ልጆችን ለማስተማርና የጤና ኢንሹራንስ ለማግኘት ይጠቅመዋል።
የብሔራዊ መታወቂያ በሦስቱም ምሰሶዎች ላይ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ነው ያሉት አቶ ዮዳሄ፣ እንደ ሀገር ብሔራዊ መታወቂያ ያወጡ ዜጎች መጠን 30 ሚሊዮን መድረሱን ገልጸዋል።
ፋይዳን በ5 ዓመት ጊዜ ውስጥ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መቶ በመቶ ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ሐሳብ፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ ከባለሀብት እስከ ጉሊት ነጋዴዎች ድረስ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አካታች ሥርዓት መሆኑን ገልጸዋል።
በላሉ ኢታላ