ኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ስትራቴጂያዊ አጋርነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡
በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሼህ ሻክቡት ቢን ናህያን አል ናህያን ጋር ውይይት አድርገዋል።
የሥራ ኃላፊዎች በሀገራቱ መካከል ያለውን ትስስር በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በታዳሽ ኃይል፣ በመሰረተ ልማት፣ እና በቴክኖሎጂ ይበልጥ ለማስፋፋት በሚቻልባቸው አዳዲስ አማራጮች ዙሪያ መክረዋል።
በወቅታዊ ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ የተወያዩት ኃላፊዎቹ፤ በአፍሪካ ቀንድ እና በመካከለኛው ምስራቅ ሰላምን፣ መረጋጋትን እና ብልጽግናን ለማስፈን ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።
የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሼህ ሻክቡት ቢን ናህያን አል ናህያን፤ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) እንድታስተናግድ በመመረጧ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ በመተግበር ላይ ያለችው የአረንጓዴ ልማት አጀንዳ ለቀጠናውም ሆነ ለዓለም አርዓያ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ረገድ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ከኢትዮጵያ ጎን በአጋርነት እንደምትቆም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች በቅርብ ወራት ውስጥ የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባን በማካሄድ እንዲሁም የከፍተኛ አመራሮችን የጉብኝት ልውውጥ በማጠናከር ስትራቴጂያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በውይይቱ ተስማምተዋል።