Search

ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የንግድ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር እየሠራች ነው - ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ

ቅዳሜ ታኅሣሥ 18, 2018 358

ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላት የኢኮኖሚ ትብብር ከቡና ንግድ ባለፈ እሴት በተጨመረባቸው ምርቶች እና በኢንዱስትሪ ትስስር ላይ እንዲያተኩር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ ተናገሩ።
ፕሬዚዳንቱ በቻይና-ኢትዮጵያ የኢኮኖሚና የቡና ንግድ ማስተዋወቂያ ኮንፈረንስ ላይ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ እና የቻይና የማይበገር ስትራቴጂካዊ አጋርነት ወደ ላቀ የኢንዱስትሪ ሽግግር እንዲያመራ በትብብር ይሠራል።
ትብብሩ በግብርና፣ በአረንጓዴ ልማት እና በቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ላይ ትኩረቱን በማድረግ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ሽግግር ለማፋጠን ያለመ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ አመላክተዋል።
በተለይም የቻይና ከተሞች ያላቸውን የኢንዱስትሪ አቅም ከኢትዮጵያ የልማት ፍላጎት ጋር በማጣመር ዘላቂ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመፍጠር የታለመ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መኖሩን አስታውቀዋል።
ይህ ዓይነቱ ትብብር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የንግድ ሰንሰለት ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራት የሚያስችል መሆኑን ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ ጠቁመዋል።
በቻይና-አፍሪካ ትብብር ማዕቀፍ ውስጥ፤ ግብርና እና ገጠር-ተኮር አረንጓዴ ልማት፣ ንግድ፣ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት እና የትራንስፖርት ትስስር ወደ ሰፊ የኢንዱስትሪ ሽግግር የሚያደርሱ መንገዶች እንዲሆኑ የጋራ ራዕይ መሰነቁን አክለው ገልጸዋል።