ኢትዮጵያ ለቻይና ገበያ የምታቀርበው የቡና ምርት ሁለቱን ሀገራት ያላቸውን ግንኙነት እንደሚያጠናክረው በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ገለፁ።
የኢትዮጵያ ቡናን በቻይና ገበያ የበለጠ ለማስተዋወቅ ገበያ ለመፈለግና ኤክስፖርቱን ለማሳደግ አላማ ያደረገው ኮንፈረንስ በቻይና ሁናን ግዛት መካሄዱን ቀጥሏል።
በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው በዚሁ መድረክ ላይ የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት እያደገ መሆኑን አንስተው፤ ቡናም ይህንን ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክረው አፅንኦት ሰጥተው ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን የገለፁት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢፋ ሙለታ (ዶ/ር) በግብዓት፣ በውጤታማ የምርት አሰባሰብ፣ ክምችትና ሥርጭት መስኮች ከቻይና ጋር ተባብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳላትም ተናግረዋል።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው ቡና ለኢትዮጵያ ምርት ብቻ ሳይሆን ባህላዊ እሴትም መሆኑን በመግለፅ የሁለቱን ሃገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያግዝ አንስተዋል።
የቻይና ገበያ ለኢትዮጵያ ቡና ያለው ፍላጎት እያደገ መምጣቱን የገለፁት የቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ይህም ለኢትዮጵያ ትልቅ እድል መሆኑን አስረድተዋል።
በቀጣይም ውጤታማ ትስስር ለማድረግ ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን ገልፀዋል።
በቻይና ሁናን ግዛት ጁጆ ከተማ በተዘጋጀው ኮንፈረንስ ከ700 ሺ በላይ ሰዎች የኢትዮጵያን ባለልዩ ጣዕም ቡና ለማስቀመስ እቅድ ተይዟል።
ቻይና የኢትዮጵያ ቡና ዋና መዳረሻ እየሆነች የመጣች ሲሆን፣ የዛሬ አምስት ዓመት የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት ከነበረችበት 33ኛ ደረጃ በተያዘው ዓመት ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ብላለች።
ይህንን የበለጠ ለማሳደግና ወደ ቻይና የሚላከውን የቡና ኤክስፖርት መጠን ከፍ ለማድረግ ነው የአሁኑ ኮንፈረንስ የተዘጋጀው።
ኢትዮጵያ ባለፈው አመት ከ 35 ሺ ቶን በላይ ቡና ለቻይና ገበያ አቅርባለች።