ታዋቂው የፋይናንስ ባለሙያ እና የ "Rich Dad Poor Dad" መጽሐፍ ደራሲ ሮበርት ኪዮሳኪ፣ የአሜሪካ ዶላር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን በመግለጽ ለዓለም ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ኪዮሳኪ የብሪክስ አገራት "ዩኒት" (The Unit) የተባለ በወርቅ የተደገፈ አዲስ የክፍያ መሣሪያ ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ ዶላርን የሚያከማቹ ሰዎች ተሸናፊ መሆናቸው አይቀርም በማለት ነው ያስጠነቀቁት።
ኪዮሳኪ በኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ገጻቸው ባስተላለፈው መልዕክት፣ የአሜሪካ ዶላር ዋጋው ተሟጦ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የዋጋ ግሽበት ሊከሰት እንደሚችል ገልጸዋል።
"ባለሀብቶች ንቁ መሆን አለባቸው፤ ዶላርን ያስቀመጣችሁ ሰዎች ሀብታችሁ በሙሉ ሊጠፋ ይችላል" ሲሉም ነው መክራቸውን የለገሱት።
ይልቁንም ይላሉ ሮበርት ኪዮሳኪ ባለሀብቶች ሀብታቸውን ወደ ወርቅ፣ ብር፣ ቢትኮይን (Bitcoin) እና ኢቴሪየም (Ethereum) እንዲቀይሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ምንም እንኳን ኪዮሳኪ "ዶላር አከተመለት" ቢሉም፣ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ግን ሁኔታውን በተረጋጋ ሁኔታ ገልጸውታል።
ፕሪዝዳንት ፑቲን "እኛ ዶላርን እየተዋጋን አይደለም፤ ነገር ግን ዶላርን እንደ ፖለቲካዊ መሣሪያ እየተጠቀሙበት ስለሆነ አማራጭ መፈለግ ግዴታችን ነው" ብለዋል።
ብሪክስ በአንድ ጀምበር አዲስ ገንዘብ ከመፍጠር ይልቅ፣ በአገር በቀል ገንዘቦች መገበያየትን እንደሚያስቀድሙ ፕሬዝዳንቱ አረጋግጠዋል።
በሰለሞን ገዳ