በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉ ስታርታፖች በኢትዮጵያ እየተፈጠሩ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ዙሪያ ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም ባለፉት 5 ዓመታት በስታርታፖች አማካኝነት ከ40 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩ ነው የተገለጸው።
አምስት ሺህ ዲጂታል ስታርታፖችን በ2030 ለማውጣት የታቀደ ሲሆን፣ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የስታርታፕ አዋጅ ወጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሆነ ተጠቁሟል።
አዋጁ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የስታርታፕ ማዕከል ማድረግ የሚያስችል ስለመሆኑም ነው የተነገረው።
ዲጂታልኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን እውን ለማድረግ ፈጠራን ማዕከል ያደረጉ ችግር ፈቺ ውጤቶች ከስታርታፖች እንደሚጠበቅ ተመላክቷል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ አመርቂ ውጤት መመዝገቡ የተገለፀ ሲሆን፣ ዲጂታል ሉዓላዊ የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።
በፍሬሕይወት ረታ