Search

አዲስ አበባን ስሉጥ ከተማ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያስገኙ ነው - የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ

ማክሰኞ ታኅሣሥ 21, 2018 93

አዲስ አበባ የስሉጥ ከተማ (Smart City) መገለጫ የሆኑ ዘመናዊ ተቋማት ባለቤት እንድትሆን እና የታለሙ ራእዮችን እውን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው እንደገለጸው፣ ተቋማት አገልግሎታቸውን በማዘመንና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለተገልጋዩ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።
በሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዘንድ ይስተዋል የነበረውን እንግልትና የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን የጠቆመው ቢሮው፤ በተለይም የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን ከሰው ንክኪ ነፃ በማድረግ፣ ፍትሃዊና ግልጽነት የሰፈነበት አሠራር ለመዘርጋት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አመላክቷል።
ይህ በቴክኖሎጂና በመሠረተ ልማት የታገዘ ሥራ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹና ዘመናዊ በማድረግ ረገድ የጎላ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ተገልጿል።
ለተገኘው ውጤት እንደ አብነት በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ በወሳኝ ኩነት ምዝገባ፣ በጤና ተቋማት፣ በንግድ ፈቃድ አሰጣጥና በገቢ አሰባሰብ ሥርዓት ላይ የተከናወኑ የዲጂታል ማሻሻያዎች ተጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በትላንትናው ዕለት የተመረቁት ዘመናዊ የፖሊስ ማዕከላትን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎታቸውን በቴክኖሎጂ በማዘመናቸው፣ የሕዝብ እንግልትን ከመቀነስ ባለፈ የሀብትና የጊዜ ብክነትን ማስቀረት እንደተቻለ ቢሮው አመልክቷል።
አዲስ አበባን ስሉጥ ከተማ ለማድረግ የተጀመረው ራእይ በአሁኑ ወቅት በርካታ የሕዝብ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ የታገዙና የተቀናጁ እንዲሆኑ በማድረግ ከተማዋን ለኑሮ ምቹና ለሥራ ተስማሚ እንድትሆን ማስቻሉ ተገልጿል።
የከተማ አስተዳደሩ ሁሉንም የልማት አማራጮች በመጠቀም ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ቢሮው አስታውቋል።